WolloPedia

WolloPedia Organic Wollo

01/09/2026

ስለ ወሎ ያልሰማችኋቸው እውነታወች

* በአማራ ክልል አካባቢወች ውስጥ የኤሌክትሪክና ስልክ አገልግሎትን ቀድሞ በማግኘት ወሎ ቀዳሚው ነው። #ደሴ ከተማ ከክልሉ ከተሞች ውስጥ ስልክ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማግኘት ቀዳሚዋ ነች።

* ባቲ፣ ትዝታ፣ አንቺ ሆዬ እና አምባሰል የሚባሉት አራቱ የኢትዮጲያ የሙዚቃ ቅኝቶች መሰረታቸው ወሎ ነው (ሌሎች ኢትዮጲያውያን ወገኖቻችን ደስ እንዲሰኙባቸው ምክንያት መሆናችን ደስ አሰኝቶናል)።

* በአማራ ክልል ውስጥ ቀዳሚው ዘመናዊ ትምህርት ቤት የተጀመረው ወሎ ደሴ ላይ ነው።

* በኢትዮጲያ እስልምና ታሪክ ውስጥ ስማቸው ገናና ሆኖ የሚታወቁት እነደ ዳና፣ ጥሩ ሲና፣ ሾንኬ፣ ጫሊ፣ ገታ፣ ደገር ወዘተ አይነት መድረሳወች የሚገኙት ወሎ ውስጥ ነው።

* ኢትዮጲያዊ የሆነው መንዙማ የተጀመረው በወሎ ነው

* በአማራ ክልል ከሚገኙ ጥንታዊ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ እጅግ ጥንታዊ የሆነችው እና ቀደምቷ ተድባበ ማርያም የምትገኘው በወሎ ነው።

* አማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከ1000 ዓመት በላይ እድሜ ካስቆጠሩ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ በግርድፉ ከ70% በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በወሎ ውስጥ ነው።

* የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ አማኞች በታላቅ ክብር ከተለያየ የኢትዮጲያ ክፍልና ከአለም ተሰባስበው ለሃይማኖታዊ የሚታደሙባቸው ግሸን ደብረ ከርቤ እና ቅዱስ ላሊበላ የሚገኙት በወሎ ነው።

* ኢትዮጲያን ለዘመናት የገዟት የዛጉዌ፣ የሰሎሞናዊ፣ የወረሴህ እና የማመዶች ሥርወ መንግስታት የተመሰረቱት በወሎ ነው። መራ ተክለ ሃይማኖት፣ ዓጤ ይኩኖ አምላክ ፣ አባ ሴሩ ጓንጉል፣ አባ ጂቦ መሀመድ አሊ የተሰኙት የእነዚህ ሥርወ መንግስታት መስራቾች ከዚሁ ከወሎ ምድር የተፈጠሩ ናቸው።

* የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የአገው እና የአርጎባ ህዝቦች በወሎ ውስጥ ይገኛሉ ።

* በዘመናዊ የኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ የወሎየወች ከፍታ የሚባለው አቤቶ እያሱ ስልጣን ሲወርሱ አባታቸው ሚካኤል ዓሊ ንጉሠ ጽዮን ተብለው የወሎ፣ የጎንደር ፣ የትግሬና የጎጃም የበላይ ገዥ ሲባሉ ነው።

* ከአማራ ክልል አካባቢወች ግንባር ቀደም በመሆን የአክስዮን ማህበር ያቋቋሙት ወሎየወች ናቸው። የወሎ ፈረስ ትራንስፖርት አክስዮን ማህበርን በእነ ፊታውራሪ አመዴ ለማ አማካኝነት በግንባር ቀደምነት ተመስርቷል።

* ወሎ የበርካታ ማዕድኖች መገኛ እንደሆነ ይነገራል። የብረት፣ የድንጋይ ክሰል ፣ የነዳጅ ፣ የወርቅ ፣ የከበሩ ድንጊያወችና ላይም ስቶን ወዘተ እምቅ ሀብት አለው።

* የተከዜ ወንዝ መነሻ ወሎ ውስጥ ነው። ለአባይ ገባር የሆነው ታላቁ በሽሎ እና የአዋሽ ገባር የሆነው ቦርከናም ከወሎ የተለያዩ አካባቢወች የሚነሱ ናቸው።

30/08/2026
 #ጥርሷ!!!!ከድጆ ከሜዳው....በሪጋው መሀከል፤በተርታ በተርታ፤ ሳቅ እየታደለ፤ደሴ አረብ ገንዳ ላይ...ፍልቅልቅ የሚለው፤ የዚነት ሙሃባ፤ጥርሷ ሰው ገደለ።የነ ሙሃባ ልጅ...እኔም ወደ እሷ...
29/08/2026

#ጥርሷ!!!!

ከድጆ ከሜዳው....
በሪጋው መሀከል፤በተርታ በተርታ፤ ሳቅ እየታደለ፤
ደሴ አረብ ገንዳ ላይ...
ፍልቅልቅ የሚለው፤ የዚነት ሙሃባ፤ጥርሷ ሰው ገደለ።

የነ ሙሃባ ልጅ...
እኔም ወደ እሷ አልሄድ፤ እሷም አትመጣ፤
ፈሽረክ ያለች ጊዜ....
ከንፈሯ በድንገት ደርሶ እየተቆጣ፤
አቦ ምን በወጣኝ...
ሳቅ አየህ ተብየ፤ በአበጋር ሸንጎ ፊት፤ነፍሴ ምትቀጣ፤

እሷም ገምሻራ ናት፤እከተላታለሁ፤ እንደው ጥሎብኝ፤
ከንፈሬና ጥርሴ ከሚጣሉብኝ፤
ብላ ጥላኝ ሄደች፤እኔም አልመጣብህ፤እንዳትመጣብኝ።

ባትመጣም ግዴለም...
ባልሄድም ግዴለም፤ብየ ነበር እኮ ያኔ ስትቆጣ፤
አዳ ምን ዋጋ አለው ...
አላስተኛኝ አለ....
ምሃተኛው ጥርሷ...
እንደ ዘብ ወታደር፤ እየቀሰቀሰኝ ሌሊት እየመጣ።

( #ገጣሚ፤ )

እንኳን ለደማቁ የአሸንድዬ፣ ሶለል እና ሻደይ የበዓል ቀናት አደረሳችሁ▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬ይህ ከነሀሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው ድንቅ የልጃገረዶች ትዕይንት በወሎ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ...
22/08/2026

እንኳን ለደማቁ የአሸንድዬ፣ ሶለል እና ሻደይ የበዓል ቀናት አደረሳችሁ
▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬▬
ይህ ከነሀሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው ድንቅ የልጃገረዶች ትዕይንት በወሎ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ትውፊታዊ ባህል ነው። የአሸንድዬ/ሻዳይ/ ሶለል በዓል ወልዲያን ጨምሮ በየጁ፣ በራያ፣ በዋግ እና በላስታ አውራጃወች እንዲሁም በዋድላ አካባቢ የሚከበር የልጃገረዶቻችን ባህላዊ ጨዋታ ቢሆንም ወንዶችም በጉጉት የሚጠብቁት ደማቅ ባህል ነው። ይህ ባህል በአንዳንድ አካባቢወች በዓለምአቀፋዊ ተጽእኖም ሆነ በማህበረሰቡ ቸልተኝነት እየደበዘዘ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት እየታየበት ነው።

የአንድ ማህበረሰብ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ማህበረሰቡ ሲወርድ ሲዋረድ ይዞት የመጣው ትውፊታዊ ባህሎች ቅድሚያውን ይይዛሉ። የአሸንድዬ/ሻደይ/ሶለል ትውፊታዊ ባህል ለዘመናት የተለያዩ ሕዝቦች የፈጠሩት መስተጋብር ሳይበግረው ዛሬ ድረስ የወሎ ማኅበረሰብ ክፋይ ለሆኑት ለራያ፣ ዋግ፣ የጁ፣ ላስታና ዋድላ አካባቢ ማህበረሰብ ታላቅ መገለጫ ለመሆን በቅቷል።

እንደ ወሎ ማህበረሰብ ተቆርቋሪነትና ያገበኛል ባይነቱ የወሎ ኅብረት ይህን የሻደይ/ሶለል/አሸንድዬ የልጃገረዶች ጨዋታ የወሎ ሕዝብ አንጡራና ቱባ ባህሉ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም ባህሉ እንዳይደበዝዝና ትውፊታዊነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ማህበራችን በከፍተኛ ትኩረት የሚንቀሳቀስበት አንዱ ዋና ጉዳይ ነው።

የዘንድሮው በዓል የደመቀ እንዲሆን በሚከበርበት አካባቢ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን በትውፊቱ መሰረት እንዲጫወቱ መገፋፋትና ሞራል መስጠት የሚገባቸው ሲሆን ልጃገረዶችም ሆነ ጎረምሶቹ ተወዳጁ በዓላቸው እንዳይጠፋ በንቃት መሳተፉ አለባቸው። ስለ በዓሉ አከባበርና ተያያዥ ነገሮች የሚያወሳውን የወንድማችን የብሩክ አበጋዝን ሀተታ እንደሚከተለው ጋብዘናችኋል።

አሸንድዬ/ሻደይ/ሶለል by: Brook Abegaz
-----------------------------
ይህ የልጃገረዶች በዓል በላስታ፣ በዋግ፣ በራያ፣ በተወሰኑ የየጁ አካባቢወች እንዲሁም በተምቤንና እንደርታ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። አሸንድዬ ልጃገረዶች በየሰፈራቸው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቤት ለቤት እየዞሩ በጭፈራ፣ በዘፈን፣ በውዳሴ ሰውን እያወደሱ ለተወሰኑ ቀናት ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ድግስ ደግሰው በድልቂያ በዘፈን ድግሳቸውን የሚበሉበት የሚቦርቁበት ባህል ነው። በዋግ ሻደይ ሲባል፣ በላስታ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢወች አሸንድዬና አሸንዳ፣ በየጁ እና በተወሰኑ የራያ አካባቢወች ደግሞ ሶለል ይባላል።

በእኔ ከተማ ልጃገረዶች አምረውና አሸብርቀው የሚታዩት ከጥምቀት ይልቅ በአሸንድዬ ወቅት ነበር። ነሀሴ ሲገባ ጀምረው ልጃገረዶች እርስ በእርስ እየተገናኙ በየእድሜ እርከናቸው ከአቻወቻቸው ጋር ቡድን መስርተው የአሸንድየው ቀን ነሀሴ 16 እስኪደርስ ድረስ ልባቸው ስቅል ብሎ ይከርማል። ልጃገረዶቹ ለአሸንድዬው ቀን በወገባቸው የሚያስሩት የተጎነጎነ ቅጠል "የአሸንድዬ ቅጠል" የሚባል ሲሆን፤ ይኼ ቅጠል በበጋ ወራት የማይገኝ ሲሆን፣ የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በመብቀል በአሸንድዬ ወቅት ለበዓሉ መድረሱ አስገራሚ ያደርገዋል።

የዋዜማው እለት አሸንድየውን ካለበት ቦታ ቆርጠው ካመጡ በኋላ በወገባቸው ልክ በገመድ/በማሰሪያ ከጎነጎኑት በኋላ ለጧት እንዳይጠወልግ ጤዛ ሳር ላይ ያሳድሩታል። በነገታው ልጃገረዶች ከቻሉ አዲስ አለበለዚያም ደግሞ የነበራቸውን ልብሶቻቸውን አጥበው ለብሰው፣ ጠጉራቸውን በሚችሉት መልኩ አበጃጅተው፣ እስከቻሉት ድረሰ በሚገባ አምረው እና ተቆነጃጅተው አሸንድዬ፣ ወፌይላላ እያሉ ሲጨፍሩ ሲዘሉ ይውላሉ። ልጃገረዶች ቀን ቀን የተጎነጎነውን አሸንድዬ ወገባቸው ላይ አስረው በየመንደሩ እየዞሩ የሚጨፍሩ ሲሆን፤ ማታ ማታ ደግሞ የተጎነጎነውን አሸንድዬ ከወገባቸው በመፍታት በሚቀጥለው ቀን ላለው ጭፈራ እንዳይጠወልግ ጤዛ ውስጥ ያሳድሩታል።

አሸንድዬ ባይ ልጃገረዶች ወደሚያወድሱት ቤት ሲገቡ አውጫዋ ልጅ ስትል ተቀባዬቹ ብለው በህብረት ያዜማሉ። ከዚያ አሸንዳዬ፣ ወፌ ይላላ እየተባለ ዜማው/ዘፈኑ ስጦታውን እስኪቀበሉ ድረስ የተለያዩ የውዳሴ ስንኞች እየተቋጠሩ እንደሚከተለው ይቀጥላል።

አሸንዳዬ
አሃ
አሸንዳ ሆይ
ሽርግፍ አትይሞይ
አሸንዳ ሙሴ
ፍስስ በይ በቀምሴ

አበሙሴ አንቺ አበሙሴ
ሽርግፍ በይ በቀሚሴ

አሸንዳዬ አሸንዳ አበባ
ጠብ እርግፍ እንደ ወለባ

ምድር ጭሬ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ
እሰይ የእኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ

ከሰፌድ ላይ አተር ኮለሌ ኮለሌ
የኔማ እሜቴ አንገተ ብርሌ

ወዘተ ግጥሞችና ስንኞች እየተደረደሩ ጨዋታው ከደራ በኋላ ስጦታውን ሲያገኙ ምስጋናቸውን እንደሚከተለው

ትሻል እሜትዬ ትሻል
ይሻል ጌትዬው ይሻል

በማለት ይገልጣሉ።

በልጅነታችን ልጃገረዶች አሸንድዬ ሲሉ አንዳዶቻችን ወንዶቹ ከልጃገረዶቹ ወገባቸው ላይ ያለውን አሸንድዬ መንጨት በጣም ከሚያስደስተን ነገር አንዱ ነበር። በተለይ ከሰፈራቸው ውጭ የሚመጡትን ልጃገረዶች አሸንድዬ በመንጨት ባዶ ስናስቀራቸው የሚሰማን ጀብደኝነት ለየት ያለ ነው፤ አሸንድያቸውን ከወገባቸው ነጭቼ ያስለቀሰኳቸው ልጃገረዶች አሁን ድረስ ትዝ ይሉኛል (ያው በልጅነት ተንኮል መስራት የደስታ ምንጭ ነው)።

አንዳንድ አሸንድዬ ባይ ቡድኖች ከእንደዚህ አይነት ነገር ራሳቸውን ለመከላከል ዱላ እና ጅራፍ ይዞ ነጭወችን የሚከላከል ፈርጠም ያለ ልጅ ያስከትላሉ። በዚህን ጊዜ አሸንድየውን የሚነጭ ልጅ ካለ ጦርነቱ የሚሆነው ከባለ ዱላው እና ከባለ ጅራፉ ጋር ነው። አንዳንዴም የሰፈራችንን ልጃገረዶች አሸንድዬ ሌሎች እንዳይነጩባቸው ለመጠበቅ እኛም እንከተላቸዋለን።

ከተለያየ ሰፈር የመጡ የልጃገረዶች ቡድኖች ሲገናኙ በሜዳየ መጣሽ ተባብለው አሽንድያቸውን ይነጫጫሉ። በእኛ ከተማ ልጃገረዶች ላይ ቀበሌና ታች ቀበሌ በሚል ከሁለት ቡድን ተከፍለው ቅልጥ ባለ ሁኔታ አሸንድየ ሲጫወቱ እንዳደጉ እናቴ ነግራኛለች። እኔን ስትወልድ አሸንድየ ማለት እንዳቆመች ያጫወተችኝ አይረሳኝም፤ ምክንያቱም ሴት ልጅ ካገባችና ከወለደች ጨዋታው ላይ መሳተፍ ስለማትችል ነው። ልጃገረዶቹም ለትዳራቸው የሚያጫቸው ሰውም በግላጭ የሚያያቸው በዚህ የአሸንድየ ወቅት ነው።

አሸንድዬ ሲጨፍሩ በቤተሰብ ባል ታጭቶላቸው ድፎ ዳቦና በግ ከአማቶቻቸው በእለቱ የሚመጣላቸውም አይጠፉም። የአሸንድዬ ወቅት ደስ ከሚሉኝ የዓመቱ ጊዚያት አንዱ ነው፤ የክረምቱ ዝናብ እየቀለለ መሄዱ፣ ክረምቱ የሚፈጥረው ልምላሜ የተዋበ መሆኑ፣ የወንዞቹ ጥራት እና በየቦታው ከሚፈነዱት ምንጮች ጋር ተያይዞ የሚማርክ ጊዜ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የአሸንድዬው ጨዋታ፣ የቡቸ/ቡሄው፣ የሆያሆየው ድግስ ወዘተ ጋር ተደምሮ ልዩ ጊዜ ያደርገዋል።

ለልጃገረዶች መልካም በዓል ይሁንላችሁ

የታሪክ አምባ - መቅደላመቅደላ አምባ ለመድረስ ከደሴ ከተማ በስተምዕራብ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የተንታ ከተማ የሁለት ሰዓት የእግር መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ጥንት ከመቅደ...
30/07/2026

የታሪክ አምባ - መቅደላ

መቅደላ አምባ ለመድረስ ከደሴ ከተማ በስተምዕራብ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የተንታ ከተማ የሁለት ሰዓት የእግር መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡

ጥንት ከመቅደላ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደ ጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚያዘልቅ በሀገሬውም፣ በውጭ ሀገር ጎብኝዎችም የሚታወቅ የእግር መንገድ ነበር፡፡ አሁን ላይ ስለዚህ መንገድ በውል የሚያውቅ እምብዛም የለም፡፡

ስለ መቅደላ ሲነሳ አጼ ቴዎድሮስ ይታወሳሉ። የመቅደላ አምባ ዙሪያ ገባውን ከረጅም አድማሳዊ ርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችል በመኾኑ እና በዘመኑ የፖለቲካ ጂኦግራፊ ሁነኛ ሥፍራ ላይ በመገኘቱ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ነበረው፡፡

አጼ ቴዎድሮስ ከጎንደር በኋላ የሥልጣን ማዕከላቸውን ለጊዜው ወደ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደ መቅደላ በማዞር ለተቀረው ግዛት አርዓያ ሊኾን የሚችል የአሥተዳደር ሥርዓት ለማቆም ጥረት የጀመሩት በዚሁ ሥፍራ ነበር፡፡

በርካታ እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ብዛት ያላቸው ገድሎች፣ መጻሕፍት እና ድርሳናት፣ እንዲሁም የንጉሡ የግል የክብር ዕቃዎች በሥርዓት ተሰድረው ይቀመጡ የነበረው በመቅደላው ግምጃ ቤት ነበር፡፡
የመቅደላው አሥተዳደር ኀላፊም ከንጉሡ የቅርብ ባለሟሎች እና የረጅም ጊዜ ወዳጆች መካከል አንዱ የነበሩት ደጃች አለሜ ነበሩ፡፡

በዘመኑ 15 መድፎች፣ 7 ሞርታሮች፣ 11 ሺህ 63 የተለያዩ ጠመንጃዎች፣ 875 ሽጉጦች እና 481 ሳንጃዎች፣ ከ555 የመድፍ እና የሞርታር አረሮች እንዲሁም 83 ሺህ 563 የተለያዩ ጥይቶች ጋር በመቅደላ የንጉሥ ግምጃ ቤት እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች ያወሳሉ፡፡ አሁን ከእነኝህ የጦር መሳሪያዎች ለታሪክ መዘከርነት በሥፍራው የሚገኘው ሴባስቶፖል የተባለው የንጉሡ ትልቅ መድፍ ነው፡፡

መጻሕፍቱ፣ ድርሳናቱ፣ የወርቅ እና የብር ዋንጫዎች፣ አክሊሎች እንዲሁም ሌሎች የንጉሡ የግል ሀብቶች የነበሩ ቅርሶች ከመቅደላው ጦርነት እና ከአጼ ቴዎድሮስ እረፍት በኋላ በደላንታ ሜዳ ላይ ለጨረታ ተሰጥተው የጠላት ሠራዊት ተቀራምቷቸዋል፡፡ ከእነኝህ ቅርሶች ከፊሉ በእንግሊዝ ሀገር በሚገኙ የተለያዩ ሙዚየሞች ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡

በመቅደላ አካባቢ ሊጎበኙ የሚችሉ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች መካከል በአጼ ላሊበላ ዘመን ከአንድ አለት ተፈልፍሎ እንደተሠራ የሚነገርለት የፉል አምባ ጊዮርጊስ ውቅር ቤተ ክርስቲያን፣ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ይስሃቅ ዘመነ መንግሥት እንደተተከለች የሚታመነው የመቅደላ ማርያም፣ በንጉሥ ሚካኤል የተሠራው እና የንጉሡ አጽም በክብር አርፎ የሚገኝበት ተንታ ሚካኤል ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በውስጣቸውም የኢትዮጵያ ጥንታዊነት የሚዘክሩ እና የሚመሰክሩ በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ይዘዋል፡፡

ምንጭ፡- የአማራ ክልል የቱሪስት መስህብ ሀብቶች አጭር ቅኝት መጽሐፍ

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ደሴ ፋና ኤፍ ኤም 96.0

ወግዲከክፍለ ዘመን ዕድሜ በፊት ያኔ ገና ድሮ የከተማነት ጀማሬዋን አንድ ብላ አበሰረች !!ለመጀመሪያ ጊዜ የአሁኗ የወግዲ ከተማ ስትመሰረት ፊታውራሪ ዘለቀ ጋረድ የተባሉ መሪ ወደ ወግዲ ተልከ...
23/07/2026

ወግዲ

ከክፍለ ዘመን ዕድሜ በፊት ያኔ ገና ድሮ የከተማነት ጀማሬዋን አንድ ብላ አበሰረች !!

ለመጀመሪያ ጊዜ የአሁኗ የወግዲ ከተማ ስትመሰረት ፊታውራሪ ዘለቀ ጋረድ የተባሉ መሪ ወደ ወግዲ ተልከው ከቀርሳ ወንዝ ወዳ ማዶ ላይ መኳንት እየተመደበ በከተማነት ደንብ የመስፈር ስራ ተጀመረ ።

በ ሺ 9 መቶ 12 ዓመተ ምህረት የዛሬ 106 ዓመት ልዑል ራስ ካሳ በአካል ወግዲ ድረስ በመምጣት በበቅሎ ላይ ሆነው አካባቢውን እየተዟዟሩ ካዩ በኋላ ከተማዋን በግምት በአንድ ጋሻ መሬት ስፋት ከልለው የከተማዋ ገዥም ቀኝ አዝማች አልዩ እንድሆኑ ሹመት ሰጡ ።

በአንድ ጋሻ መሬት ስፋት የተጀመረ ከተሜነት በአራቱም አቅጣጫ ሜዳ ሜዳውን እየተከተለ ዛሬ ደብረ ከርቤ አፋፍ ድረስ ዘልቋል ።

በሰኔ ወር መጨረሻ ረፋድ ላይ በለስላሳ አየር ያማረው የደብረ ከርቤ አካባቢ እስከ ለሚ ድረስ ሽር ብሎ ይታይ ነበር ። ልጁም ይሄን ሁኔታ ተመስጦበት ቢጠሩት አይሰማም ።

መልካም ቆይታ !!

Gashaw Mekonnen

ከላላከወለቃ ወንዝ ወዲያ ማዶ ከላላን አሻግሪ እየተመለከትኳት ነው ። ከላላ በቀድሞ ስሟ ገፈርሳ እየተባለች ነበር የምትጠራው ።አሊ በለው ፦ አካባቢው እስትራቴጂካዊ ቦታ ሆኖ ቢያገለግላቸው  ...
22/07/2026

ከላላ

ከወለቃ ወንዝ ወዲያ ማዶ ከላላን አሻግሪ እየተመለከትኳት ነው ። ከላላ በቀድሞ ስሟ ገፈርሳ እየተባለች ነበር የምትጠራው ።

አሊ በለው ፦ አካባቢው እስትራቴጂካዊ ቦታ ሆኖ ቢያገለግላቸው " ይህ ጥሩ ከላላ ነው ። " ብለው በመናገራቸው በዚሁ መነሻነት ገፈርሳነቷ ቀስበቀስ እየቀረ ከለላ በሚል ስያሜ መጠራት ጀመረች ።

አሊ በለው እንድህ ተብሎላቸው ነበር ።

አሊ በለው መጣ ቦረና ደረሰ
የፈረሱን ጭራ እየነሰነሰ
የአሊ በለው ፈረስ አይበላም ገለባ
ልቤ ገሰገሰ ወደ አደስ አበባ ።

አሁንም ከወለቃ ወንዝ ወዲያ ከላላን እየተመለከትኳት ነው ።

በአከባቢው በትልቅነቱ የሚታወቀው የወለቃ ወንዝ አንዳንዴ እየጎደራ ፤ አንዳንዴ ደግሞ እየተገማሸረ ሲጓዝ ይታያል ።

ወለቃ ከቦቶ ወንዝ ጋ ሲገናኝ ከላላን ሽቅብ እየከመከመ የሰሜን ሸዋን ጫፍና የወግዲን ኩታ ገጠም ቁልቁል ተከትሎ ወደ እናቱ አባይ ሆድ ውስጥ ይገባል ።

በሌላ በኩል ደግሞ ሙቀጭ ፣ ጉናና ገረዋ ፊታቸውን ለጀምበር መግቢያ ሰጥተው ከወለቃ
ወድህ ማዶ ያለውን ለሚና ጫቀታን ይመለከቱታል ።

አሻግሬ ዙሪያ ገባውን ስቃኝ ከጉና በስተጀርባ ከተራራው ወዳ ሸንተረሩን ወርዶ የሚገኘው አቤት ውሃ ( መርሳ) ውል አለብኝ ።

በተመሳሳይ መንገድም የሀሳብ ጉዞዬን ስቀጥል .... የመረቆን ወንዝ ተሻገሬ ከአድማስ ወዳ ማዶ ወዳለው ሀገረ ደገር ገባሁ ። ይህ የደገር መስጂድ ነው ።

Gashaw Mekonnen

Adresse

Vienna

Webseite

Benachrichtigungen

Lassen Sie sich von uns eine E-Mail senden und seien Sie der erste der Neuigkeiten und Aktionen von WolloPedia erfährt. Ihre E-Mail-Adresse wird nicht für andere Zwecke verwendet und Sie können sich jederzeit abmelden.

Service Kontaktieren

Nachricht an WolloPedia senden:

Verknüpfungen

Teilen