
10/08/2025
በመስዕዋትነት የመሰረትነውን ድርጅት ለመሸርሸር መሞከር፤ በደም የዘጋነውን በር መነቅነቅ ዋጋ ያስከፍላችኋል!!
ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ መግለጫ
""""""""""""""""''"""""""""""""""""""""""""'"""""""
ነሐሴ 04 ቀን 2017 ዓ.ም
የአማራ ፋኖ በጎጃም በአማራ ህዝብ ታሪክ ውስጥ የአብዮት ሐሳብ በግንባር ቀደምትነት ያፈለቀ ፤ በመራር መሰናክል አልፎ የትጥቅ ትግል ያዋለደ ፤ ህዝብ በመቀስቀስ ፣ በማደራጀት ፣ በማሰልጠን ፣ በማስታጠቅ በአረመኔው አገዛዝ ሰራዊት ላይ የሐይል እና የፖለቲካ ብልጫ የወሰደ ፣ የአማራን የመከራ ቀንበር ከህዝባችን ትክሻ ላይ ለማውረድ በግንባር ቀደምትነት ዋጋ እየከፈለ ያለ ግዙፍ ድርጅት መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው ።
ይህ በመስዕዋትነት ላይ የቆመ ህዝባዊ ክብር ፣ በጀግንነት የተገነባ መዋቅር ፣ በበሳል አመራሮች የሚመራ ድርጅት የሚያደርገው የድል ግስጋሴ ቀን እረፍት ሌት እንቅልፍ የሚነሳቸው ፀረ አማራ ሐይሎች ትናንት በድርጅታችን የአማራ ፋኖ በጎጃም ውስጥ ሰርጎ በመግባት የማፍረስ ተልኳቸው አልሳካ ሲላቸው ዛሬ በሐይል ድርጅቶችንን የመረበሽ ተልኳቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ ።
ከሰሞኑ ራሱን ወሎ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ብሎ የሚጠራው ሐይል በፋንታሁን ሙሀባ እና በማስረሻ ሰጤ መሪነት ከጋይንት በመነሳት በዳውንት አድርጎ ደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት እና ከለላ ወረዳወችን በማለፍ በቦረና ሳይንት መካነሰላም አካባቢ የነበረውን የሀቀኛ ታጋይ ፋኖወችን ካምፕ አጥቅቶ እና ተቆጣጥሮ ይህንን ወታደራዊ ቤዝ በማድረግ ዓባይን በመሻገር ምስራቅ ጎጃም መርጡለማርያም ያለውን የዓባይ ሸለቆ ብርጌድን ለማጥቃት ያለመ እንቅስቃሴ አድርጓል ።
የአማራ ፋኖ በጎጃም ይህንን አፍራሽ እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ከመከታተል ጎን ለጎን ጠላትን ሳይሆን እኛን ሊታገል ያሰፈሰፈውን ፀረ-ትግል ቡድን ከአፍራሽ እንቅስቃሴው እንዲቆጠብ እና ትግል የሚፈልጉ ከሆነ በሰላማዊ መንገድ እንዲቀላቀሉን ጥሪ ሲያደርግ ቢቆይም ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ቦረና ሳይንት ወረዳ ሆኖ ዓባይን አሻግሮ ወደ ቀጠናው ተኩስ በመክፈቱ የአፀፋ ምላሽ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ስለሆነም ድርጅታችን ጉዳዩን ከዚህ በላይ መታገስ ስለማይችል ይህ ቡድን ወሎ-ቦረና ሳይንት ወረዳ ውስጥ ቢሊ ፣ በታ ፣ ዶክስ እና ወከሌ በተባለ ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ እያለ የአማራ ፋኖ በጎጃም የዘጠነኛ ሳሙኤል አወቀ ክፍለጦር አባይ ሸለቆ ብርጌድ በወሎ ቀጠና ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ወንድሞቻችን ጋር በመቀናጀት በወሰደው እርምጃ በበታ፣ በዶክስ እና በወከሌ አካባቢዎች የነበረውን ይህንን ሐይል ከአካባቢው አፅድቷል ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጥቂት ግለሰቦችን በየዋህነት የሚከተለው ታጋይ ላይ ሰብዓዊ ጉዳት ላለማድረስ ሲባል እና የመካነሰላም እና አካባቢውን ማህበረሰብ ላለመረበሽ ሲባል በጥንቃቄ በተከናወነ ኦፕሬሽን 15 የቡድኑ አባላትን ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ስር በማዋል የአባይ ሸለቆ ብርጌድን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
በአሁኑ ሰዓት ፋንታሁን ሙሀባ እና ማስረሻ ሰጤ የቀራቸውን ሐይል ይዘው በደቡብ ወሎ ደንቆሮ ጫካ እና አህዮ በተባለ ቦታ አድርገው ሸሽተዋል። ከቡድኑ ተነጥለው በየቦታው የተበታተኑ ልጆችን የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸው ከድርጅታችን እንዲቀላቀሉ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን።
በመሆኑም አፋጎ ከሀቀኛ የፋኖ ወንድሞቻችን ጋር በመቀናጀት ድርጅቱን እና ትግሉን መጠበቁን የሚቀጥል መሆኑን እያሳወቅን እነኝህ ከቀጠና ቀጠና እየዞሩ የትግላችን ሐዲድ ላይ ለመቆም የሚሞክሩት ቡድኖች ከመሰል አደገኛ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን!!!
አዲስ ትውልድ! አዲስ አስተሳሰብ! አዲስ ተስፋ