07/27/2025
"ካልተናገሩት አይታይ ብልሃት፣ ካልታረደ አይታወቅ ስባት" የሚባለው ወጋችን ጭብጡ ጠንካራ ነው:: ለዚህ እምቅ ባለአቅም አባባል ምሳሌ ይሆን ዘንድ አንድ ባለሃሳብ 'ኢትዮጵያን ወደተረጋገጠ ሰላም ለማምጣት ከሁሉም በፊት በማንኛውም መንገድ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከሥሩ ገርሥሶ መጣል ነው" ቢልና፣ ለምናልባቱም የተናጋሪውን የፖለቲካ ሸፍጥ የክት መነጋገሪያ ይሆን ዘንድ ወደ ጎን አቆይተን፣ ይህን ጠንካራ ሃሳብ ወለድ መደምደሚያ እንደ አንድ ቅን ዜጋ የሃሳብ አምክንዮና ፍላጎት ወስደን ብንነሳ ተናጋሪው ግለሰብ ብዙ ያላሰላሰለውና ያላገጣጠመው ብልሃታዊ ጎደሎ እንዳለው በሌሎች ዘንድ ሊስተዋል ይችላል::ይህ ተናጋሪ መንግሥትን ገርሥሶ መጣልን ግብ አደረገው እንጅ እንዴት ከዚያ መድረስንና በምን አይነት የተሻለ መንግሥት ለመተካት "እንደተዘጋጀ"-ከጣሉ በኋላ ስለተኪው ማሰብ ሳይሆን እንደ ሀገር ለመፅናት የነበረው ሲነሳ ወዲያውኑ ከነበረው መንግሥት የባህሪ ልክ በላይ የሚያሟላና የሕዝብንና የሀገርን ደኅንነት ኃላፊነት ወስዶ የሚተካ አዲስ ስንዱ አካል ያስፈልጋል፣ ያለዚያ አስተማማኝ መደገፊያ የሌለው ፍላጎታችን መደምደሚያ አድርገን በማስተጋባት ለባሰ አደጋ እንዳረጋለንና- አጠንጥኖ አላወቀም:: በሀገር ጉዳይ ላይ አማርጦና መርጦ፣ ተገጣጥሞ የሚያያዝና ወደ ፈለጉት አቅጣጫ በመፍሰስ መዳረሻውን የሚያመለክት አቋም መያዝ ካልተቻለ የስሜታችንና የፍላጎታችን ግብዓት መጨረሻው አንድም ወደ እርስ በርስ እልቂት መግባት ነው፣ አሌያም ከመጋረጃው ጀርባ ተደብቆ እየተዘጋጀ ለሚጠብቅ፣ ሀገርንና ታሪክን ለሚያጠፋና የበለጠውን ክፉ ለሆነ በለሃሰብ አስረክቦ ባዶ እጅን ማጨብጨብ ይሆናል::