04/02/2026
"ታላቁ አልከሶ መስጅድ እና መውሊድ "
ታላቁ የአልከሶ መስጅድ የሚገኘው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ አስተዳደር ሲሆን ከዞኑ ዋና ከተማ ወራቤ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 8 ኪ/ሜ ርቀት ለይ ይገኛል ።
መስጂዱ በትውልድ ቅብብሎሽ በከሊፋ የሚተዳደር ሲሆን የኢስላማዊ አስተምህሮ ማዕከል በመሆን ለ127 ዓመታት ኢስላማዊ አስተምህሮን በማስቀጠል የእውቀት ሽግግር ማዕከል በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
ከስልጤ ቀደምት ሀይማኖታዊ መሪዎች አንዱ ለሆኑት አልከስዬ መታሰቢያነት የተገነባው ጥንታዊና የብሄረሰቡን የግንባታ ጥበብና ፍልስፍና የሚያንፀባርቅ መስጅድ ነው።
ታላቁ የአልከሶ መስጅድ በአሰራሩም ሆነ ባለው ታሪካዊ፣ በህላዊና ሀይማኖታዊ ገፅታ ታዋቂነትን ያተረፈ ጥንታዊ መስጅድ ሲሆን መስጅዱ የተሰራበት 3 ሜትር መጠነ ዙሪየ ያለው ምሶሶ ከረጅም ርቀት በሰው ጉልበት ተጎትቶ ለመምጣት የተደረገው ጥራትና የሚነገረው አፈታሪክ እንዲሁም ከምሶሶው የሚነሱ ወጋግራዎች ጥንታዊትና ታሪካዊነት ውስጡን ገብቶ የሚጎበኝ ሰው ሳይደነቅባቸው ከማያልፋቸው ቅርሶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።
መስጅዱ የተገነባበት የእንጨት ምሰሶዎች ከሥፋራው ከ80 ኪ.ሜ ርቀት ከሚገኝ ልዩ ስሙ ጎልጆ ከሚባል ቦታ በሰዎች ሸክም የመጣ ስለመሆኑም በአከባቢው የሚኖሩ አባቶች ይነገራሉ ፡፡
ከመስጅዱ ጥንታዊና ታሪካዊናት በተጨማሪ አከባቢውን ለመጎብኘት ቱሪስቶች በሚመጡበት ወቅት በአስጎብኝዎች የሚነገሩ አስገራሚ አፈ-ታሪኮችና ገጠመኞች በርካታ ናቸው ።
ታላቁ የአልከሶ መስጅድ ከስልጤ ቀደምት ኃይማኖታዊ መሪዎች አንዱ ለሆኑት አልክስዬ መታሰቢያነት የተገነባ ጥንታዊ መስጂድ ሲሆን በየአመቱ የረመዳን ፆም ከመግባቱ 15 ቀን ቀደም ብሎ የሚዘጋጅ ታላቅ የመውሊድ በዓል ይስተናገድበታል፡፡
ከ1 መቶ 30 በላይ እድሜ እንዳለው የሚነገረው ታላቁ የአልከሶ መስጅድ ከቱሪስት መስህብ ስፍራነቱ በተጨማሪ በመውሊድ በዓል ከአካባቢው የሙስሊም ማህበረሰብ በተጨማሪ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በጥንታዊ መስጂዱ በመሰባሰብ በአንድ ኢማም ሰላት የሚሰገድበት፣ ዱአ የሚደረግበት አባቶች ምዕመናኑን የሀገራችሁን ሰላም ጠብቁ፣ ሥራ ስሩ፣ የሰውን ላብ አትንኩ፣ የላባችሁን ብቻ ውደሱ በማለት የሚመክሩበት ነው ።
የአከባቢው ማህበረሰብ እምነቱን፣ባህሉንና ወጉን ለዘመናት ጠብቆ እንዲቆይ የአልከሶ መውሊድና በስፍራው የሚሰጠው እስላማዊ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ይናገራል ።
መስጂዱ የስልጤ ብሄረሰብን የስነ-ጽሁፍና ስነ-ጥበብ የሚያሳዩ ባህላዊ የመፃፊያ መሰሪያዎችና ጥንታዊ ከእንጨትና ከብረት የተሰሩ ቅርሶችን ጨምሮ ጥንታዊ የሆኑ ሀይማኖታዊ መጽሐፍት ይገኙበታል ።
በታላቂ የአልከሶ መስጅድ የሚከበረው የአልከሶ መውሊድ ታላቁ የረመዳን ፆም መቃረቡን ለማሳወቅ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ለ119ኛው ግዜ ተከብሯል ።
jr