
02/03/2025
የአርበኛ ዘመነ ካሴ የዓድዋ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት ፦
አድዋ የቅኝ ግዛትን ጨለማ ድል ነስቶ የበራ የእኩልነት እና የነጻነት አብሪ ኮኮብ ነው ። አድዋ በአባቶቻችን አጥንትና ደም የተሰራ ገዘፍ ያለ የእኩልነት ሃውልት እና ወደር ባልተገኘለት የዚያ ዘመን ትውልድ የሞራል ልዕልና የተበጀ ፍልስፍናም ነው። አድዋ የእነ አጤ ምኒልክ የእጅ ስራ ነው ። አባቶቻችን አድዋን የሰሩት ከአድዋ በበለጠ የአዕምሯቸው ምጥቀት ፣ የሀሳብ ርቅቀት ሲሆን በኢትዮጵያ ያልተቋረጠ የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ አድዋ በአደራረጉም ይሁን በውጤቱ ህያው ምሳሌና መመሪያችን ነው።
አድዋን ስናከብር ፣ አባቶቻችን ስንዘክር ከነጻነት ራስጌው የነበርን እኛ ለፍጹም አምባገነን ስርዓት እና በህልውና አደጋ ውስጥ የተገኘነው ለምን እና እንዴት ነው ? የሚለውን ጥያቄ በመመርመር መሆን አለበት ። ለምንገኝበት ሁለንተናዊ ውድቀት ምክንያቱ ለአድዋ የሚመጥን ስርዓትና መዋቅር መገንባት ያለመቻላችን ነው ። ከአድዋ በሚቃረን አስተሳሰብ ላይ የቆመ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ነጻነትና እኩልነት ሊቀበልና ሊያከብር አይቻለውም።
መላ ኢትዮጵያን ለመከራ የዳረገው ፣ የአማራን ህዝብ ደግሞ የማጥፋት ጦርነት የከፈተበት የአገዛዙ ገዥ አሰተሳሰብ ጸረ-አድዋ ፣ ጸረ-እኩልነት እና ፍጹም አረመኔ ነው ። ለኢትዮጵያውያን ባለው ንቀት እና የመግዣ ስልቱ በሆነው የማጭበርበር ዘዴው የተነሳ አድዋን በቃላት በማሽሞንሞን የአድዋ ወዳጅ ለማስመሰል ቢጥርም በግብሩ የአድዋን የነጻነት መንፈስ ለመረዳት የማይችል እቡይ መሆኑን አረጋግጧል ።
ትግላችን ለነጻነት ፣ ለእኩልነት ከሁሉም በላይ ደግሞ ለህልውና የምናደርገው ነው ። ትግላችን ከአድዋ አባቶቻችን በወረሰነው የላቀ የሞራል ልዕልና የሚመራ ነው ። ትግላችን በድል እንደምናጠናቅቅ የእጃችን መዳፍ ያህል እርግጠኞች ሆነን የምናውቀው ነጻነት እና እኩልነት በባርነት የሚረቱበት ፣ የሞራል ጥራትም በእቡይነት የሚመከትበት ታሪክም ሆነ ሳይንስ ስለሌለ ነው ።
በመሆኑም ትግላችን የተከፈተብንን የህልውና ጦርነት ድል አድርገን ለአድዋ የሚመጥን ስርዓትና መዋቅር በመገንባት የህዝባችን መብቶችና ጥቅሞች በቋሚነት በማስከበር ይሆናል ።
ከአድዋ አባቶቻችን የምንማረው አንዱ ቁም-ነገር በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችን ሁሉ ወደ ጎን በመተውና ለጊዜው በማቆየት በዋናው ጠላታችን ላይ ማበር ያለብን መሆኑን ነው። ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ በአንድነት እንድንሰለፍ ጥሪያችን እናቀርባለን።
እንኳን ለ 129ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ ።
አዲስ ትውልድ ፣ አዲስ አስተሳሰብ ፣ አዲስ ተስፋ !
አርበኛ ዘመነ ካሴ ባውቄ