22/03/2026
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከሩሲያ ጎን ሆነው የሚዋጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ”1,800″ ማለፉ ተነገረ።
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት አራተኛ ዓመቱን የተሻገረ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሩሲያ ጎን ሆነው በቅጥረኛ ተዋጊነት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ዞብል ፖስት ያገኘው መረጃ ያሳያል።
ለሩሲያ በተዋጊነት የሚመለመሉ ኢትዮጵያውያን አብዛኛዎቹ ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች እንደሆነ መጽሔታችን ያገኘው መረጃ የሚያሳይ ሲሆን፣ ባለፉት አራት ዓመታት ከ1 ሺህ 8 መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሩሲያ ጎን ሆነው በጦርነቱ መሳተፋቸው ተነግሯል።
አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ለሩሲያ ለመዋጋት የተፈራረመ ኢትዮጵያዊ ለዞብል ፖስት እንደገለፀው፣ ከትውልድ ቀየው ከአማራ ክልል ወደ ሩሲያ ለመጓዝ በቅድሚያ 800 ሺህ የሩሲያ ሩብል ወይም 10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደተከፈለው የገለፀ ሲሆን፣ በየወሩ ደግሞ 200 ሺህ የሩሲያ ሩብል ከሩሲያ መንግሥት እንደሚከፈለው አሳውቋል።
ግለሰቡ አክሎም ከሩሲያ ጎን ሆነው የሚዋጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ከ1 ሺህ 8 መቶ በላይ መድረሱን የጠቆመ ሲሆን፣ ከትግራይ ክልል ውቅሮ አካባቢ፣ ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ሮቤ አካባቢ፣ እንደዚሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት ፀጥታ መዋቅር ከድተው ለቅጥረኛ ተዋጊነት ወደ ሩሲያ የሄዱ ኢትዮጵያውያንን እንደሚያውቅ አያይዞ ገልጿል።
ኢትዮጵያውያኑ ለቅጥረኛ ተዋጊነት የሚመለመሉት በራሳቸው ፈቃድ እና የሦስተኛ ወገን ተፅዕኖ ሳይኖርባቸው እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በምታደርገው ጦርነት ሲሳተፉ ግን የሩሲያን ሕግ ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እንደሚገደዱ ታውቋል።
ዝርዝሩን ለማንበብ! 👇
https://zobelepost.com/ethiopians-fighting-for-russia-in-the-war-with-ukraine/
ከስራ በተያያዘው ሊንክ የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
https://t.me/zoblePost