01/09/2026
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የተማሪዎች የእርካታ ዳሰሳ ጥናት 1ኛ ደረጃ ወጣ።
ነሀሴ 26/2018፣ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የሪፎርም ስራዎች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የትምህርት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው ። ባለፋት ዓመታት በተጀመሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሪፎርም ስራዎች፣ በአጋር አካላት እርካታ፣ በመውጫ ፈተና፣ በድህረ-ምረቃ ተማሪዎች የትምህርት ወጪ ፣በተመራቂ ተማሪዎች የመቀጠር ምጣኔ፣ እና መሰል የሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የከፍተኛ ትምህርት ገባዔ ከነሐሴ 25 እስከ 27 /2018 ዓ/ም እየተካሄደ ሲሆን በጉባዔው የዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ ም/ ፕሬዝዳንቶች እና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
በአረንጓዴ ግቢው፣ በፍፁም ሠላማዊነቱ እና በተመራጭ ፕሮግራሞቹ የሚታወቀው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት በተካሄደው የተማሪዎች የእርካታ ዳሰሳ ጥናት (Students' satisfaction Survey) አንደኛ ደረጃ በመውጣት በተማሪዎች ተመራጭ እና ተወዳጅ መሆኑን አረጋግጧል ።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 1ኛ ደረጃ የወጣበት የተማሪዎች የእርካታ ጥናት በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች የሚያቀርቧቸው የምኝታ እና የምግብ አገልግሎቶች ፣ የትምህርት ጥራትን፣ የአመራር እና የመምህራንን ተደራሽነት፣ የግቢውን ውበት እና ምቹነት ፣ የግቢውን ሠላም እና ደህነት መሠረት ያደረጉ መለኪያዎችን ባካተተ ጥናት ነው።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ አጭር እድሜው ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ግቢውን ለተማሪዎች እና ለሰራተኞች ማራኪ እና ምቹ ለማድረግ ባካሄዳቸው መጠነ-ሰፊ የግቢ ውበት ስራዎች እና ባስፋፋቸው የአካዳሚክ ፕሮግራሞች በተማሪዎች ግንባር ቀደም ተመራጭ እየሆነ የመጣ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ይታወቃል።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በ2019 የትምህርት ዘመን በሰባት ኮሌጆች ማለትም በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፣ በምህንድስና እና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ፣ በተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ፣ በትምህርት እና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ፣ በማህበራዊ እና ሰባዊ ሳይንስ ኮሌጅ እና በግብርና ኮሌጅ እንዲሁም በህግ ትምህርት ስር በተደራጁ በ61 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ያስታወቀው ዩኒቨርስቲው በ2018 የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያመጡ ተማሪዎች እንጅባራ ዩኒቨርሲቲን የመጀመሪያ ምርጫቸው እንዲያደርጉት ጥሪውን አስተላልፏል።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲን ቀጥሎ ኦዳቡልቱም እና ወልዲያ ዩኒቨርስቲዎች በተማሪዎች የእርካታ ዳሰሳ ጥናት 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ይዘዋል።