
24/11/2024
በወላይታ ዞን የከፍተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት የሚሰጡ 4 ጤና ጣቢያ ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ
ህዳር 15 2017 የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ በአቶ ፀጋዬ ኤካ የተመራው የባለሙያዎች ቡድን በዳሞት ፑላሳ እና ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ከወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እና ከጤናው ዘርፍ አመራሮች ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀዶ ህክምና ብሎኮችን ሥራ ማስጀመሪያ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
በዞኑ የከፍተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት የሚሰጡ 4 ጤና ጣቢያ ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ አስታውቀዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተገበራቸው ካሉት በርካታ ስራዎች አየተሰሩ መሆኑንና የዚሁ ግብ አንድ አካል የሆነው በቀዶ ህክምና የማዋለድ አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት የእናቶችና የጨቅላ ህጻናት ሞትን መከላከል ትኩረት የተሰጠው ተግባር እንደሆነ አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡
የቀዶ ህክምናን ተደራሽነት ለማሻሻል እስካሁን 8 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች በገጠር ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደር አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የገለጹት ሀላፊው የቀዶ ህክምና ብሎኮች በሚገኙ በአዴ ሻንቶ፣ ጋራ ጎዶ፣ ጉኑኖ እና ሆብቻ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል ግብአትና የሰለጠነ የሰው ሃይል ተሟልተው አገልግሎት እንዲጀመሩ ከዞን አስተዳደር እና አክሲስ ከተሰኘ አጋር ድርጅት ጋር በጥምረት ክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ነው የመምሪያ ሀላፊ የተናገሩት።
ከጤና ጣቢያዎቹ 5 ጠቅላላ ሀኪሞች በቀዶ ህክምና እንዲያዋልዱ የሚስችል የክህሎት ስልጠና በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ከዞን አስተዳደር፣ ወረዳ አስተዳደር፣ ከተማ አስተዳደር እንድሁም ከሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ግብአት የማሰባሰቡ ሥራ በማጠናቀቅ በቀጣይ አንድ ወራት ውስጥ ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የመምሪያ ሀላፊ ገልጸዋል።