27/10/2025
የማይረቡ ነገሮች ላይ ውደቁ ብሎ የፈረደብን ማን ይሆን ? ደጋግሜ የምላችሁ ሰይፉ ፋንታሁን ይህ ነው ።
==================================
(ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)
ትናንት በሰይፉ በኢቢኤስ ከቀረቡ ፕሮግራሞች የእነዚህ ሁለት ልበ ብርሀን ህጻናትና ከሰውና ከብረት ተቀላቅላ የተሰራችው እናታቸው ጉዳይ ትኩረቴን ስቦታል ። በጣም ተገረምኩ ። የተገረምኩት ግን ለእነዚህ ልጆችና ለእናታቸው በተደረገው አይደለም ። ከእሱ በላይ እኛ ትኩረት የምንሰጥበት ርዕሰ ጉዳይ ልዩነት ይገርማል ። ትልቁን ጉዳይ ቸል ብለን ረብ የለሹ ላይ መንጠላጠላችን " ምን ሆነን ነው ? " ያስብላል ። ሰይፉ ፋንታሁን እነዚህን ልጆች ወደ ሚዲያው ከማምጣት ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ተሰብስቦ የዓይናቸው ህክምና ጉዳይ ተጀምሮ ህክምናውን ቢያገኙም ውጤቱ ሳይሳካ ቀርቷል ። ሰይፉና አድናቂዎቹ ፣ የፕሮግራሙ ቤተሰቦችና በሰይፉ በኢቢኤስ መልዕክቱ የደሰረሳቸው ሁሉ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል ።
ወዳጃችን ሰይፉ ፋንታሁን የእነ ሶሊያናን ጉዳይ እንዲሁ የአንድ ፕሮግራም አየር መሙያ አድርጎ አልተወውም ። ብረቷ ሴት በችግር እንዳይፈታ " ከፕሮግራሙ ተከታታዮች " ጋር ተባብሮ የመኖሪያ ቤት ኪራይ እንዳያስቸግራት ቪላ ቤት ፣ ልጆቿን ከቤት ት/ቤት ወይም አስፈላጊ ቦታ መውሰጃና መመለሻ እንዳይቸግራት ዘመናዊ መኪና ፣ ቤትና መኪና ቢኖራትም እሱ ብቻውን መተዳደሪያ ስለማይሆን ኬክ ቤት ከፍተው ሰጧት ። አንድ ጉርሻ እና 1,000.00 ብር የሰጠ ሁሉ በቴሌቪዥን እየቀረጹ ተረጂዎቹን መከራ በሚያሳዩበት በዚህ ጊዜ ሰይፉ ፋንታሁን ቢደመር ከ10,000,000.00 ብር በላይ የሚያወጣን ስጦታ በቀልድና በጨዋታ አዋዝቶ ትልቁን ጉዳይ እንደ ቀልድ ነው ያለፈው ። ሰይፉ ፋንታሁ አይናገረውም እንጂ " አንዳንድ የፕሮግራሜ ተመልካቾች " እያለ ለተቸገሩ ከሚሰጠው ጥቂት የማይባለውን ራሱ ሰይፉ ፋንታሁን ከኪሱ እያወጣ የሚያደርገው ነው ። እዚህ የቤት ፣ የመኪናና የኬክ ቤት ስጦታ ላይ ሰይፉ ፋንታሁን ቀላል በማይባል ደረጃ እንደሚኖርበት አምናለሁ ።
አስባችሁታል ለእነዚህ ቤተሰቦች እንደ ቀላል የተሰጣቸው ቤት ፣ መኪና እና ኬክ ቤት ነው ። የሰውን ሕይወት የሚያነሳው አንድ አምላክ ቢሆንም ሰይፉ ፋንታሁን ስድስት ሆነው አንድ ክፍል ውስጥ ተደራርበው ይተኙ የነበሩ ሰዎችን ነው የየራሳቸው ክፍል እንዲኖራቸው ያደረገው ። ሦስት ታማሚ ልጆቿን ባልተመቻቸ ሁኔታ ታንቀሳቅስ የነበረች ሴት ናት ድንገት የራሷ መኪና የኖራት ። ምንም አይነት መተዳደሪያ ያልነበራት፣ ምናልባትም ልጆቿን ኬክ መጋበዝ የሚቸግራት ሴት ናት ድንገት ኬክ ቤት የኖራት ። ይህ ተዐምር ሆኖ ሳለ ፣ ካሁን ቀደም በየትኛውም የሚዲያ ተቋም ያልተደረገ ሆኖ ሳለ የፌስቡኩ ቤተሰብ ምንም ሳይለው ( ምናልባት ጥቂቶች አንስተውት ቢሆን እንጂ ) ያለፈው ። ከእሱ ይልቅ የእነዚያ አታካች ጥንዶች ወሬ ትኩረት ተሰጥቶታል ። ራሱ ሰይፉ እነዚህን ጥንዶች ከዚህ ታላቅ ተግባር ጋር ደብሎ ማቅረቡ ልክ አልነበረም ።
የማህበራዊ ሚዲያው ቤተሰብ ምን ትኩረቱን እንደሚስበው ይታወቃል ። ዩቱዩብ ላይ ተመልካች ለማግኘት ካልሆነ እነሱን ማቅረብ ቢያንስ የትናንቱን ሰይፉ በኢቢኤስን አይመጥንም ። እኔ በግሌ ምንም ቢሉ ላያቸው ፈቃደኛ አይደለሁም ። እውነት ግን እንደ ህብረተሰብ ምንድነው የነካን ? የማይረቡ ነገሮች ላይ ውደቁ ብሎ የፈረደብን ማን ይሆን ? እንዴት ከወራት በፊት ማህበራዊ ሚዲያውን በትኩረት የወጠረው ሙሉ ቤተሰብ ሕይወት በአንድ ፕሮግራም ምክንያት ፈርሶ የመሰራት ያህል ሲለወጥ እንዴት ምንም ሳይመስለን ቀረ ? በመካካድ አጀንዳ መሆን የሚፈልጉን ተመሳሳይ ጠባይ ያላቸው ጥንዶች እንዴት እነሱ ትኩረታችንን ሳቡት ?
እንዴት ሰይፉ ፋንታሁንን ከልባችን አላመሰገነውም ? ይህ እኮ አንድ ፕሮግራም ሳይሆን ዓይናችን እያየ የተሰራ ተዐምር ነው ። ኮሚቴ ተዋቅሮና የወራት ሩጫን ጠይቆ ፣ ሚዲያውን አጭሶ በትልቅ መርሐ ግብር የሚደረገውን ስጦታ እኮ ነው ሰይፉ ፋንታሁን እንደዋዛ ሰጥቶ ዞር ያለው ። እንዴት እሱ በባለውለተኛነት ባይጮህ እኛ " እናመሰግንሀለን " አንለውም ። ይገርማልም ፣ ያሳዝናልም ። ወንድም ዓለም ሰይፉ ፋንታሁ ፋንታሁን በቃላት ላመሰግንህ አልችልም ። እግዚአብሔር ስራህን ይየው ። በራስህ ብቻም ሳይሆን በትዳርህና በልጆችህ ይከፈልህ ።