
10/10/2024
"ነገር ያበላሻሉ፣ እሳት ይጭራሉ"- መንግስት የቀድሞ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴን
"እኔን አይሰሙኝም፣ አይረዱኝም"- ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ መንግስትን
(መሠረት ሚድያ)- የስራ ግዜያቸው የተጠናቀቀው ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዛሬው እለት በዲፕሎማቱ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተተክተዋል።
የፕሬዝደንቷ ለቀጣይ የስራ ዘመን እጩ ሆኖ አለመቅረብም ሆነ እርሳቸው ለመቀጠል አለመፈለጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል።
ከትናንት በስቲያ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ አንድ ፅሁፍ የኤክስ (ትዊተር) አካውንታቸው ላይ ካጋሩ በኋላ በርካቶች የተለያዩ ግምቶችን ሲያስቀምጡ ነበር። አንዳንዶች አካውንታቸው ሀክ ተደርጎ ወይም ተጠልፎ ሊሆን ይችላል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ጉዳዩ እንደዛ ሳይሆን ፕሬዝደንቷ ለአመታት በመንግስት ሲገፉ ቆይተው በመጨረሻም በይፋ መተንፈሳቸው ነው ብለው አስተያየት ሲሰጡ ተመልክተናል።
በዚህ ዙርያ እስካሁን በብቸኛነት በይፋ አስተያየት የሰጡት የፕሬዝደንት ፅ/ቤት ሀላፊው አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ ሲሆኑ እሳቸውም "የፕሬዝደንት ሳህለ-ወርቅ ኦፊሴላዊ አካውንት አለ፣ እኛ አስተያየት መስጠት የምንችለው በእሱ ዙርያ ነው። የተባለው ፅሁፍ በግል አካውንት ላይ ስለተለጠፈ ቢሯችንን አይመለከትም" በማለት ኢትዮጵያ ቼክ ለተባለው ለመረጃ አጣሪ ተቋም ምላሽ ሰጥተው ነበር።
ይህን ክስተት ተከትሎ መሠረት ሚድያ ምንጮቹን ጠቅሶ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመጪው ጥቅምት ወር ላይ የሚጠናቀቀውን የስራ ዘመናቸውን ተከትሎ በርዕሰ ብሄርነት መቀጠል አንደማይፈልጉ፣ መንግስትም እጩ እንደማያደርጋቸው ዘግቦ ነበር።
ይሁንና ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ የስራ ዘመን በርካታ አስተያየቶችን ያስተናገደ ሆኗል።
አንዳንዶች ሀገሪቱ ጦርነት ላይ በነበረችበት እና ሰላም ያስፈልጋል ብሎ መናገር ሀጥያት መስሎ ይታይበት በነበረበው ግዜ ጭምር ስለ ሰላም መናገራቸውን በማንሳት ያወድሷቸዋል። ይህ በወቅቱ ያደረጉት የሰላም ጥሪ ከስራ አስፈፃሚው አካል ጋር ለነበራችው ቅያሜ አንዱ መነሻ እንደነበር የሚጠቁሙ መረጃዎችም አሉ።
በሌላ በኩል ፕሬዝደንቷ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው በጦርነት ሲረግፍ ያላቸውን የመንግስት የስራ ድርሻ በመጠቀም በበቂ ሁኔታ ህዝብን ደግፈው አልቆሙም፣ ብዙ ግዜ የዳር ተመልካች ነበሩ እንዲሁም ግፍ ለሚፈፅሙ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከለላ የሰጡ ናቸው በማለት ይከሷቸዋል።
በንግግራቸው ሁለት ግዜ "ቀይ መስመር ተጥሷል" ብለው የሚያውቁት ኘ/ት ሳህለወርቅ በተለይ የሰሜኑ ጦርነት ወቅት በጀመረበት እለት "ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲባል ልናሰምረው እና ልናከብረው የሚገባን ቀይ መስመር ተጥሷል፡ አገራችንን ካንዣበበባት ክፉ አዳጋ ለማዳን ሁላችንም ሚና አለን፡የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው፡ቀይ መስመር መጣስ የለበትም እንበል" በሚለው ንግግራቸው ይታወሳሉ።
"ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ በስራ ገበታቸው እያጋጠማቸው ያለ ችግር ነበር ወይ?" በማለት አብረዋቸው ለሰሩ እና አሁንም እየሰሩ ላሉ፣ ስማቸውን ግን በጥያቄያቸው መሰረት ለማንገልፃቸው ሰዎች ጥያቄያችንን ከመሠረት ሚድያ አቅርበን ነበር።
አንደኛው ምንጫችን ጉዳዩን ሲያብራሩ ፕሬዝደንቷ ወደ ስልጣን በመጡ ሰሞን፣ በተለይ በ2011 እና 2012 ዓ/ም ላይ የፕሬዝደንትነት ስራን ብቻ ሳይሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስራን ጭምር ደርበው ሲሰሩ ነበር ይላሉ። ለማሳያም ፕሬዝደንቷ ኢትዮጵያን ወክለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጠቅላላው ጉባኤ ላይ በመገኘት በ2012 ዓ/ም ንግግር ያደረጉበትን ግዜ ያነሳሉ።
"ይሁንና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅሬታውን ማቅረብ ጀመረ፣ ፕሬዝደንቷ የእነሱን ስራ ጠቅልለው መስራታቸው በውጭ ጉዳይ አልተወደደም ነበር፣ መንግስት ግን ይህን እያደረገ የነበረው 50 ፐርሰንት ካቢኔውን ሴት ያረገ እና ሴት ፕሬዝደንት የሾመ መሆኑን ጭምር ለአለም ለማሳየት ነበር" የሚሉት እኚህ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ምንጫችን መንግስትም ፕሬዝደንቷን በድጋሚ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ መልሶ ልኮ እንደማያውቅ ይጠቁማሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ አለም አቀፍ ስብሳባዎች ላይ ቀስ በቀስ እንዲቀሩ እየተደረጉ እንደመጡ በማንሳት ይህም በፕሬዝደንቷ ዘንድ እንዳልተወደደ ተናግረዋል።
ይሁንና ጠ/ሚር አብይ አህመድ በወቅቱ ሳይታሰብ ወደ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ መኖርያ በመሄድ ጉዳዩን በማስረዳት ሁኔታውን ለማለዘብ ሙከራ አድርገው እንደነበር ታውቋል።
አንዳንድ ክስተቶች በዚህ ላይ ተደራርበው ነገሮችን እንዳወሳሰቡ የሚጠቁም መረጃ የሰጡን ደግሞ ሌላዋ የፕሬዝደንቷ የቅርብ ሰው ነበሩ።
እኚህ ምንጫችን እንደ ምሳሌ ያነሱት ከፕሪቶርያው ስምምነት መፈረም በኋላ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋፅኦ ያደረጉ ተብለው በርካታ ግለሰቦች እና ጦርነቱን በሁሉም ወገን ሲመሩ የነበሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደ ፕሮግራም ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሸለሙ "ሰላም ይስፈን" ብለው ተናግረው የነበሩት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ግን ገሸሽ መደረጋቸው እንዳበሳጫቸው ያነሳሉ።
"የእውቅና ፕሮግራሙን የተመለከቱት ቤታቸው ሆነው ነበር፣ ለሽልማት ቢቀር ለመሳተፍ እንኳን ጥሪ አልደረሳቸው ነበር" ብለው ወቅቱን አስታውሰዋል።
በአንድ ወቅት አርቲስት ታሪኩ ጋንኪሲ (ዲሽታ ጊና) በአንድ ኮንሰርት ላይ ስለ ሰላም መውረድ ተናግሮ ክፉኛ ከተተቸ በኋላ ፕሬዝደንቷ በነጋታው በቀጥታ አርቲስቱ ጋር በመደወል "አይዞህ፣ የተናገርከው ሁሉ ትክክል ነው፣ ያንተ ግዜ ይመጣል" ብለው እንደነገሩት ያነሱት እኚህ ምንጫችን ይህ ከአርቲስቱ ጋር ያረጉት ንግግር ግን ከፕሬዝደንት ቢሮ ሾልኮ ጠ/ሚር ቢሮ መድረሱንና ይህን ጥሩ ድባብን እንዳልፈጠረ አስረድተዋል።
ሌላኛው መሠረት ሚድያ ያነሳው ጥያቄ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ከጠ/ሚር አብይ አህመድ ጋር ስላላቸው የስራ ግንኙነት ነበር።
መጀመርያ ላይ እጅግ የሰመረ ይመስል የነበረው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ኋላ ላይ እየሻከረ እንደመጣ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን በዚህ ዙርያ ያነጋገርናቸው ሁሉም ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን ይስማማሉ።
ፕሬዝደንቷ "ነገር ያበላሻሉ" እና "እሳት ይጭራሉ" የሚል ክስ ሲቀርብባቸው እርሳቸው በበኩላቸው ደግሞ "እኔን አይሰሙኝም፣ አይረዱኝም" የሚል እሰጥ አገባ ውስጥ እንደቆዩ ትዝብታቸውን ያጋሩን ምንጮች ይህ ንትርክ ገፍቶ መጥቶ በ2016 ዓ/ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመክፈቻ ስብሰባ ላይ ፕሬዝደንቷ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ በፕሮቶኮል እና ክብር ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ ጠ/ሚሩ ፕሬዝደንቷ አዳራሽ ውስጥ እያሉ ጥለው እንዳወጡ ያስታውሳሉ።
በግል ባህሪያቸው "ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ" የሚባሉት ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ አንዳንድ ግዜ በተደጋጋሚ የመነጫነጭ እና በስራ አለመርካት አብረዋቸው ለሚሰሩ ሰዎች ፈታኝ እንደሆኑ የሚያነሱ አሉ።
"ከግል ጠባቂ ጀምሮ እስከ ፅ/ቤት ያሉ ቶሎ ቶሎ ስራ የመቀያየር ነገር አለ፣ አብሮ መስራት አስቸጋሪ ነው፣ ሰው አብሯቸው አይቆይም፣ በስራም አይረኩም" ያሉት አንድ አብረው የሰሩ እና መረጃ የሰጡን ግለሰብ ነገሮችን እጅግ በጥልቀት እና በጥንቃቄ ማየት መፈለጋቸው አንዳንዴ ስራዎችን አስቸጋሪ ያደርገዋል ይላሉ።
እንደ ምሳሌ የሚያነሱት የማህበራዊ ሚድያ ፖስቶችን እንኳን እርሳቸው አይተው፣ ፎቷቸውን መርጠው እና አሰናድተው ካልሆነ እንደማይለጠፍ ያስረዳሉ። ጥንቃቄው መልካም ቢሆንም ስራን ግን እጅግ ፈታኝ እንደሚያደርጉ የሚያነሱ አሉ። ሌላው ቀርቶ ተፅፎ የሚሰጣቸው ንግግርን በቀይ አስምረው፣ አስተካክለው እና ኤዲት አርገው እንጂ በቀጥታ እንደማያነቡ አብረዋቸው የሰሩ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በውጭ ሀገራት፣ በተለይ ለአመታት ባሰሩባቸው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት እጅግ ከፍተኛ ክብር እና አድናቆት እንደሚቸራቸው በስፋት ይነሳል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በሀገራቸው፣ በተለይ በስራ አስፈፃሚው የፖለቲካ አካል "የምለውን አይሰሙም" የሚለው አካሄድ በትናንትናው እለት በትዊተር ላሰፈሩት ፅሁፍ መዳረሻ እንደሆናቸው እነዚህ የምንጮቻችን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የፕሬዝደንቷን የትዊተር ፅሁፍ ተከትሎ አንዳንድ የሚድያ ዘመቻዎች በመንግስት ካድሬዎች እና በመንግስት ባለስልጣናት ጭምር እንደተጀመረባቸው ተመልክተናል።
ለምሳሌ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አለምፅሐይ ሽፈራው "ሀገር መምራት መታደል ነው፣ እድሉን መጠቀም ግን ጥበብ ይጠይቃል" የሚል አንድ ፅሁፍ በትናንትናው እለት በግል የፌስቡክ ገፃቸው ላይ አጋርተው የነበሩ ሲሆን ከ16 ሰአት ቆይታ በኋላ አጥፍተውታል።
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በፅሁፋቸው "ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ በታሪክ አንዴ ብቻ ሊገኝ የሚችል እድል ገጥሟት የታላቋ ሀገር ፕሬዝደንት ሆነች! ከዛን ግዜ ጀምሮ ምን ለሀገር ሰራች ብለን የምናነሳው አንድም ነገር የለም" ያሉ ሲሆን አክለውም "ፕሬዝደንቷ በቆየችበት ግዜ ይህን ማድረግ ተስኗት ቆይቷል" ብለው ለጥፈው ነበር። እኚህ የመንግስት ሀላፊ ትንሽ ቆይተው ደግሞ "ካረጁ አይበጁ" የሚል ፅሁፍ አቅርበው አሁን ድረስ በገፃቸው ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ የኢቢሲ ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ነብዩ ባዬ በቅርቡ ከፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ጋር የነበራችውን አንድ ንግግር በፌስቡክ ገፃቸው ካጋሩ በኋላ በፅሁፋቸው ወደ መጨረሻው ላይ ፕሬዝደንቷ "ለብዙ ነገር ዝምታ መልሳቸው ነበር ብዬ አላምንም። ያመኑበትን ተናግረዋል።
ዝምታ ትርጉሙ አልተቀየረምም ብዬ አስባለሁ። እኔም ባለፈው አንድ አመት ኢትዮጵያ ውስጥ ነበርኩ። እኛ ቀጥ ያሉና በግልፅ እየተናገሩ እጅግ በተጋነነ የፕሮቶኮል አጀብ የኖሩ ርዕሲተ ብሔር ድንገት ያንኑ ድምፃቸውን በሰማሁ በአንድ ቀን ልዩነት እንደዚያ ድብስብስ ያለ መልዕክት ያስተላለፉት ምን ለማለት እንደሆነ እንደሚነግሩን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለው ሀሳባቸውን አጋርተዋል።
መረጃን ከመሠረት!