
25/02/2025
ሴቶችና ክህነት
አንዳንድ ወገኖች (በተለይም ወጣቶች) በምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የሚደረገውን በማየትና የቤተክርስቲያንንም ሥርዓት ካለመጠንቀቅ (በተገቢው ደረጃ ካለመረዳት) የተነሳ “ለሴቶች ለምን ክህነት (ዲቁና፣ ቅስና እና ጵጵስና) አይሰጣቸውም?” የሚል ጥያቄን ያነሳሉ። አልፎ አልፎም ቤተክርስቲያን ለሴቶች ክህነት አለመስጠቷ ለወንዶች ስለምታደላ (ሴቶችን ስለምታገል) ነው ሲሉም ይሰማሉ። በአጠቃላይም የክርስትና አስተምህሮ፣ ታሪክ፣ አገልግሎትና ሥርዓት ወንዶች ላይ ያተኮረና ሴቶችን ያላሳተፈ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እነዚህን ብዥታዎችን ከግንዛቤ በማስገባት በዚህ ክፍል በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በክህነት ዙሪያ ሴቶችን የሚመለከተውን አስተምህሮ እናቀርባለን።
ሴቶችና ክህነት
ከሁሉም አስቀድሞ መታወቅ ያለበት ነገር ክህነት ክብር (honor) ሳይሆን የመስዋዕትነት (sacrifice) አገልግሎት መሆኑ ነው። ክህነት በሰው ምርጫ የሚገኝ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም ክህነት የሚሰጥ ኃላፊነት እንጂ የሚጠየቅ መብት አይደለም። ወንድም ቢሆን ወንድ ስለሆነ ወይም ስለተማረ ብቻ ክህነት አይሰጠውም። የክህነት አገልግሎት ሰውን ወደ ጽድቅ ቢመራም በራሱ ግን ጽድቅ ወይም የጽድቅ መስፈርት አይደለም። የክርስትና ግብም ድኅነትን ማግኘት እንጂ ክህነትን መያዝ አይደለም። ካህናት ምንም እንኳን የማሠርና የመፍታት ስልጣን ቢሰጣቸውም እንደሌሎች አገልጋዮች የቤተክርስቲያን አንድ አካል እንጂ የበላይ አካል ተደርገው መወሰድ የለባቸውም።
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናነበው እግዚአብሔር አስቀድሞ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ ብሏል። መስዋዕት በማቅረብና መሰል የክህነት አገልግሎት የሚፈፅሙትም ወንዶች ነበሩ። ዐበይትና ደቂቅ ነቢያትም ወንዶች ነበሩ። በሐዲስ ኪዳንም አስራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ አራቱ ወንጌላውያን፣ መልእክታትን የፃፉት፣ በሐዋርያት እግርም የተተኩት ካህናት ወንዶች ናቸው። በዘመናችንም ያሉት ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት በሥጋዊ ፆታቸው ወንዶች ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ዋናው ጥያቄ “ክህነት ለምን ለወንዶች ብቻ ይሰጣል?” የሚለው ነው።
የጌታችን ትምህርትና የሐዋርያት ትውፊት
በብሉይ ኪዳን ክህነት ይሰጥ የነበረው ከሌዊ ነገድ ለተወለዱ ወንዶች ብቻ ነበር። በሐዲስ ኪዳን ግን ክህነት በዘር ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ይሰጣል። ከብሉይ ኪዳኑ ውርስ ባሻገር የሐዲስ ኪዳን ክህነት ለወንዶች እንዲሰጥ መሠረት የሆነው ጌታችን አሥራ ሁለት ሐዋርያትን መምረጡና የመስዋዕትን ሥርዓትና የማሠርና የመፍታት ስልጣንን ለእነዚህ ብቻ መስጠቱ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ማርያም መግደላዊት የትንሣኤውን ብስራት ሰምታ በደስታ ጌታችንን ልትነካው ስትቀርብ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አትንኪኝ፣ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፣ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብለሽ ንገሪያቸው።” (ዮሐንስ 20:17) ማለቱ የሐዲስ ኪዳን ክህነት ዋነኛ መገለጫ የሆነው የጌታችንን የከበረ ቅዱስ ሥጋውን መንካት “ወንድሞቼ” ላላቸው ደቀመዛሙርት ተለይቶ የተሰጠ መሆኑን እንረዳለን። ይህም ቶማስ በተጠራጠረ ጊዜ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፣ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ።” (ዮሐንስ 20:27) በማለቱ የተገለጠ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በሚያውቀው ምክንያት የሐዲስ ኪዳን ክህነት ለወንዶች ብቻ የሚሰጥ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን ትውፊት በግልፅ የደነገጉት ነው።
ሴቶች ክህነትን የሚቀበሉ ቢሆን ኖሮ ጌታን በመውለዷ ከነቢያትም ከሐዋርያትም፣ ከቅዱሳን ሊቃነ መላእክትም በላይ ለከበረችው ለድንግል ማርያምና ጌታችንን በመዋዕለ ሥጋዌው ለተከተሉት 36 ቅዱሳት አንስትም ይህንን የክህነት ሥልጣን በሰጣቸው ነበር። ክህነት የአገልግሎት ድርሻ ነው እንጂ አድልኦ አይደለም። ቅዱሳን ሐዋርያትም ያስቀጠሉት ጌታ ያስተማራቸውን ሥርዓት ነው። እርሱም ያለወንድ ዘር ከሴት (ከድንግል ማርያም) ወንድ ሆኖ ተወልዶ ራሱ መስዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ ሊቀ ካህን ሆኖ ሥርዓትን የሠራው ለዚህ ነው። ድንግል ማርያም የመስዋዕቱ መገኛ፣ ጌታችን መስዋዕት ነው።
የክህነት ስልጣን በዘመን ይለወጣል?
በአንዳንዶች ዘንድ “ጌታችን ለሴቶች ስልጣነ ክህነት ያልሰጠው በወቅቱ በነበረው ባህላዊና ማኅበራዊ ምክንያቶች ነበር፣ በዘመናችን ግን ሴቶችን ከክህነት ኃላፊነት ይከለክሉ የነበሩ ባህላዊና ማኅበራዊ ማነቆዎች ስለቀነሱ ሴቶች ካህን መሆን ይችላሉ” የሚል አስተሳሰብም እንዳለ ይታወቃል። ይሁንና ይህ አስተሳሰብ በሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን ተቀባይነት የሌለው መሠረታዊ ስህተት ነው። ምክንያቱም ጌታችን ለሰዎች ባህልና ማኅበራዊ ጉዳይ የሚገዛ (የሚያደላ) ኢ-ፍትሀዊ አምላክ አይደለምና በእነዚህ ምክንያቶች ልዩነትን አይፈጥርም። በተጨማሪም በዚያን ዘመን የነበረው አስተምህሮና ሥርዓት በወቅቱ በነበረው ባህልና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ የተመሠረተ ነበር ከተባለ እምነት ለባህል ተገዢ ነው፣ ቋሚ እምነትና የእምነት ሥርዓት የለም፣ እንደየዘመኑ ባህል መለዋወጥ አለበት ወደሚል ሌላ ስህተት ይመራል።
ክህነት ለሴቶች አለመሰጠቱ ከወንዶች ያሳንሳቸዋል?
ወንዶች እንደ ሴቶች ያለ የመውለድ ጸጋ ያልተሰጣቸው ከሴቶች ስለሚያንሱ እንዳልሆነ ሁሉ ክህነት ከወንዶች መካከል ለሚመረጡ መሰጠቱም ሴቶች ከወንዶች ስለሚያንሱ አይደለም። ምክንያቱም መንፈሳዊ አገልግሎት በጸጋ የሚገኝ እንጂ የመቻል ያለመቻል ጥያቄ አይደለምና። የክህነት አገልግሎት ለመስዋዕትነት የሚገቡበት እንጅ በዘመናችን እንደምናያቸው አንዳንድ ምንደኞች ሰማያዊ ስልጣንን ለምድራዊ ኃይል ማግኛ መሰላል ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። አንድ ካህን “እግዚአብሔር ይፍታህ/ሽ” ለማለት የሚያስፈልገው ቃል ሁሉም የሚችለው ነው። ሌላውም ለክህነት የሚያበቃ እውቀት ማንኛውም ሰው (ወንድም ሆነ ሴት) ተምሮ የሚደርስበት እንጂ ፍፁም የተለየ አይደለም። የተለየ የሚሆነው እግዚአብሔር በቸርነቱ ለካህናት የሰጠው የጸጋ ስልጣን ነው። የጸጋ ስጦታ ደግሞ የተለያየ ነው። ለወንዶች ብቻ የሚሰጥ፣ ለሴቶች ብቻ የሚሰጥ፣ ለሁለቱም የሚሰጥ ጸጋ አለ። ይልቁንም ጌታችን ለሴቶች ክህነትን ያልሰጠው በሰው ተፈጥሮ ካለው ልዩነት አንጻር እርሱ በሚያውቀው ለወንጌል አገልግሎት መስፋፋት ሁሉም የየራሱ ድርሻ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር እንጂ ለማበላለጥ እንዳልሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል።
የዲያቆናዊት አገልግሎት
ለሴቶች ከሚሰጡ ከክህነት ጋር ተያያዥ የአገልግሎት ዘርፎች አንዱ የዲያቆናዊት አገልግሎት ነው። ለምሳሌ ያህል ዲያቆናዊት መሾም እንደሚገባ ፍትሐ ነገሥቱ ያዛል። ዲያቆናዊትም ሴቶችን ታስታምራለች፣ ለሴቶችም ምስጢራት ሲፈፀሙ ካህኑን ታግዛለች። በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ 17 እንደተገለጸው “ኤጲስ ቆጶስ ንጹሖችን ሴቶች መርጦ ሴቶችን ለማገልገል ዲቁናን ይሾማቸዋል። ምዕመናን ሴቶችን ለሚያስፈልጋቸው ነገር በጠሩ ጊዜ ከዲያቆናዊት በቀር ወንድ ዲያቆን ወደ ሴቶች ቤት ሊልክ አይገባውም። ስለዚህም ስለሚያጠምቋትም ሴት ሰውነትን ሜሮን ትቀባ ዘንድ ነው። ወንድ የተራቆተችውን ሴት ማየት አይገባውምና” በማለት የዲያቆናዊትን አገልግሎት ያስረዳል።