16/08/2026
''በአበሽጌ የተፈጸመው ግድያ ቀይሽብርን የሚስተካከል ነው! መሰል ግፍን በቃ ለማለትና እንዳይደገም ለአንድ ቀን እናስባቸው ''
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰጠ መግለጫ
ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጉራጌ ዞን፣ አበሽጌ ወረዳ፣ ናቻ ቁሊት ቀበሌ ሦስት ወጣቶች በማንነታቸው ተመርጠውና ከሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ላይ እንዲወርዱ ተደርገው "ፋኖ ናችሁ" በሚል ሰበብ ታሪክ እንደሚያወሳን በቀይ ሽብር ዘመን ሲደረግ ከነበረውም በላይ እጅግ ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ግድያ መፈጸሙን አረጋግጠናል።
ከአካባቢው ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሠረት የጭካኔውን ወደር የለሽነት የሚያረጋግጠው ዘግናኙን ድርጊት ፈጻሚው የፀጥታ አካል ከገደላቸውም በኋላ አስከሬናቸውን የቀብር አፈር እንዳይቀምስ በመከልከሉ በአውሬ እንዲበላ መደረጉንም ሰምተናል።
ከግፍ ሰለባዎቹ አንዱ የሆነው ይታገሱ አሰግደው ከዚህ ቀደም ወንድሙ ከሐዋሳ ተይዞ በተመሳሳይ እንዲረሸን ተደርጓል። ይህም ግድያው ቤተሰብንና ማንነትን ማዕከል ያደረገ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ይላሉ የአካባቢው ምንጮች።
በተመሳሳይ ከወር በፊት ግዛቸው ግርማ የተባለ ሌላ ወጣት በዚያው በአበሽጌ ወረዳ፣ ዳርጌ ቀበሌ በዘፈቀዳዊ መንገድ ተረሽኗል። ወጣቱ ሥራ ፈጣሪና ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል የከፈተ ብሎም በአካባቢው እጅግ ምሥጉን ነበር።
የዞኑም ሆነ ወረዳው ማኅበረሰብ በፍቅርና በመከባበር በመኖር የሚታወቅና እንደምሣሌም የሚጠቀስ ነው። አንዳንድ የወረዳ አመራሮችና የፀጥታ አካላት እያመጡት ያለው መግለጫም አደገኛና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረግ ከመሆኑም በተጨማሪ ዜጎች ምክንያት እየተፈጠረላቸው በዘፍቃድ እንዲጨፈጨፉ የሚያበረታታ መሆኑንም በግልፅ የሚያሣይ ነው።
ሰው በወንጀል ተግባር ተሳትፏል ቢባል እንኳን ለፍርድ ወደ ሕግ ቦታ ቀርቦ ፍርዱን በአደባባይ ያገኛል እንጂ ከሕግ ውጭ ዜጎችን የፊጥኝ አሥሮ በጥይት ደብድቦ መግደል የሚያሳየው ሥርዓቱ በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን አጠቃላይ የሰብዓባዊ መብት ጥሰት፣ የደቦ ፍርድና ጭካኔ መሆኑን ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት(የሦስቱ ፓርቲዎች ጥምርት) ያምናል፤ የግፍ ግድያውንም በጽኑ ያወገዛል፡፡
ለሞቱት ነፍስ ይማር እያለ ለአካባቢው ማኅበረሰብና ወዳጅ ዘመድ መጽናናትን ይመኛል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ማክሰኞ ነሐሴ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሦስቱ ወጣቶች ዘፈቀዳዊ ግድያና በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ተመሳሳይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በማውገዝ የአንድ ቀን የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ “የንጹሓን የግፍ ግድያ ይብቃ//Stop Massacre of Civilians//” በሚል ቃል እንዲያወግዝና ድምጹንም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያሰማ ጥሪ እያቀረብን፤
1.ከሕግ ውጭ ምክንያት ፈጥሮ ግድያ የፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎችና ግፉ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ አካላት ለፍትሕ አደባባይ እስከሚቀርቡ ሕዝቡ ድምጹን እንዲያሰማ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
2.ግፉን ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት እየሰጡ ያሉት የማንአለብኝነት መግለጫ እንዲቆም እያሳሰብን ግድያዎች አፋጣኝ፣ ገለልተኛ፣ ግልጽና አስተማማኝ ምርመራ እንዲደረግባቸው እንጠይቃለን።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት - ለኢትዮጵያ
ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ