17/09/2025
ለመስቀል በዓል መግቢያ ባጅ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የመስቀል በዓል መግቢያ ባጅ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ፡፡
መስከረም ፯ ቀን ፳፻፲፷ ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ የሙዚየም ዝግጅትና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋና ክፍል ለመስቀል በዓል መግቢያ ባጅ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጿል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ የሶፍት ዌር ኢንጂነሮቹ እንደ እንደ ገለጹት “እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነታችን መሥራት የሚገባንን ለማገዝ ነው የሚመጣነው የትኛውም መሥሪያ ቤት ሥራን ለማቅለል ዘመኑ በደረሰበት ዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ሥራን ለማቅለል እየተሠራ ነው፡፡ ብለዋል፡፡
“ዛሬ ይዘን የቀረብነው ዲጂታል መፍትሔ የቤተክርስቲያን ባጅ ማኔጅመንት ለመሥራት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በወረቀት፣ በእጅ በመጻፍ በብዙ ድካም ሲሰራ የነበረውን ሥራ ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ለማቅለል በቴክኖሎጂ እየሠራን ነው ሲል ኢንጂነር በቀለ ዴቢሴ ገልጿል፡፡” ባለሙያውም አክሎ ይህ ሲስተም ሁለት ነገሮችን ያቀላል የመጀመሪያው በጣም አድካሚና ጊዜ የሚፈጅ የነበረውን የወረቀት ሥራን ያቀላል፤ ሁለተኛው ተጠያቀነት ባለበት መልኩ ባጁን መቆጣጠር ይቻላል በማለት ያስረዳል፡፡
ኢንጂነር ጳውሎስ ታደሰም እንደገለጸው “ቀድሞ ይዘጋጅ የነበረው ባጅ ሴሪያል ቁጥር ብቻ ያለው ነበር፤ ባጁ ምንም እንኳ ከጀርባው ማኅተም ቢኖረውም ማንም ሰው ከለር ፕሪንተር ያለው አመሳስሎ ፕሪንት አድርጎ መግባት ይቻላል፤ አሁን ግን ኪው አር ኮድ (QR Code) ስላለው በሞባይል አፕሊኬሽን ስካን በማድረግ ባጁን መለየት ይቻላል፤ ተመሳሳይ ፕሪንት አድርጎ የሚመጣው ሰው መግባት አይችልም ሲስተሙ ያጋልጣል፡፡ በመግቢያው በር ላይም ይህን ቼክ የሚያደርጉ አሉ” ብሏል፡፡
ሁለቱም ባለሙያዎች እንደተናገሩት እንደ ቤተክርስቲያን ልጅነታችን ዛሬ የተጀመረው ሲስተም እንደ ማስጀመሪያ ትልቅ ነገር ነው በደረስንበት የሙያ ዘርፍ ቤተክርስቲያን ማገልገል፣ የቤተክርስቲያን ሥራ መማቀላጠፍ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ኃላፊ በኩረ ትጉኃን ቀሲስ ምትኩ ከንቲባ ባስተላለፉት መልእክት ባጁ በዘመናዊ ዲጂታል የተዘጋጀ ቴክኖሎጂ የሚቆጣጠረው ስለሆነ ለበዓሉ የሚመጡ ታዳሚዎችም ባጁን በጥንቃቄ ሊይዙት ይገባል ሲሉ መልእክተቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዘገባዉ የEOTC TV ነው