 
                                                                                                    20/07/2025
                                            †  ቅዳሴ ኤጲፋኒዮስ †
★ እጅግ ድንቅና ጥልቅ ምሥጢረ መለኮት ያለበት ቅዳሴ ነው አንብቡት።ለሌሎችም ሼር አድርጉት★
እግዚአብሔር በገናናነቱ ገናና ነው። በቅድስናው የተቀደሰ ነው። በምስጋናው የተመሰገነ ነው። በክብሩም የከበረ ነው።
ከመቼ ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ ነው። እስከ ዛሬ የማይሉት ማእከላዊ ነው። እስከዚህ የማይሉትም ደኃራዊ ነው።
ለአነዋወሩ ጥንት የለውም። ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም። 
ለዘመኑም ቍጥር የለው። ለዓመታቱም ልክ ቍጥር የለውም።
ለውርዝናውም ማርጀት የለበትም። ለኃይሉም ጽናት ፣ ድካም የለበትም። ለመልኩ ጥፋት የለበትም። ለፊቱ ብርሃንም ጨለማ የለበትም።
ለጥበቡ ባሕር ድንበር የለውም። ለትእዛዙም ይቅርታ መስፈርት የለውም። ለመንግሥቱም ስፋት ዐቅም ልክ የለውም። ለአገዛዙም ስፋት ወሰን የለውም።
በኅሊና የማያገኙት ሥውር ነው። በልቡናም የማይረዱት ምጡቅነው። አንሥርት የማይደርሱበት ረጅም ነው። ዓሣዎች የማይዋኙበት ጥልቅ ነው።
ከተራሮች ራስ ይልቅ ከፍ ያለ ነው። ከባሕር ጥልቅነት ይልቅ ጥልቅ ነው። ነገሥታት የምይነሣሡበት ጽኑ ነው። መኳንንት የማይቃወሙት አሸናፊ ነው።
የጥበበኞችን ምክር የሚያጠፋ ጥበበኛ ነው። የሚመክሩትን ሰዎች አሳባቸውን የሚያስረሳ ዐዋቂ ነው። የጸኑ ልጓሞችን የሚፈታ ኃያል ነው።
የኃጥኣንን ጥርሶች የሚያደቅ ፤ የትዕቢተኞችንም ክንድ
የሚቀጠቅጥ ብርቱ ነው።
የግብዞችን ፊት የሚያዋርድ ክቡር ነው። የዝንጉዎችን ብርሃን የሚያርቅ ከሃሊ ነው። ባልንጀራ የሌለው አንድ ነው።
ዘመድ የሌለው ስሉጥ ነው። ሰማያት ይጠፋሉ ፤ የብስም
ትጠፋለች ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃል። እርሱ ግን እስከ
ዘላለሙ እርሱ ነው።
የባሕር መመላለስዋ ድንቅ ነው። ድንቅስ በልዕልናው
እግዚአብሔር ነው። 
የሚመስለው የለም። ከፍጥረትም ሁሉ ከአማልክትም ሁሉ የሚተካከለው የለም። እርሱ ብቻ አምላክ ነው። እርሱም ብቻ ጌታ ነው። ፈጣሪም እርሱ ብቻ ነው። ሠሪም እርሱ ብቻ ነው።
ስላሰበው ጥበብ ረዳት አይሻም። ስለወደደውም ሥራ መካር አይሻም። ሳይሆን ቀድሞ እንደ ሆነ አድርጎ ፤ ያልተደረገውንም እንደ ተደረገ አድርጎ ሁሉን ያውቃል።
ሳይጠይቅ ኅሊናን ይመረምራል። ሳይመረምር ልቡናን
ይፈትናል። ያለ መብራት በጨለማ ያለውን ያያል።
ጻድቁን ጽድቅን ሳይሠራ ያውቀዋል። ኃጥኡንም ኃጢአት
ሳይሠራ ያውቀዋል። ልበኞችን ከአባታቸው አብራክ ሳይወጡ ያውቃቸዋል። ኃጥኣንንም ከእናታቸው ማኅፀን ያውቃቸዋል።
የሚሸሸገው የለም። የሚሠወረውም የለም። ከእርሱም የሚሠወር የለም። ሁሉ በእርሱ ዘንድ የተገለጸ ነው። በዓይኖቹም ፊት የተዘረጋ ነው። ሁሉ በመጽሐፉ የተጻፈ ነው። በሕሊናውም ሁሉ የተጠራ ነው።
ቍጥር የሌላቸው ታላላቆችን መመርመር የሌለባቸውን የተደነቁ የከበሩ ሥራዎችን ይሠራል። ሥራው ከአየነው ይልቅ ዕፁብ ነው።
ኃይሉም ከሰማነው ይልቅ ድንቅ ነው። ጌትነቱም ከነገሩን
ይልቅ ድንቅ ነው።
ከጨለማ ለይቶ ብርሃንን ፈጠረ። ደመናውን መለየት ያውቃል። ውኃውን እንደ ወደደ ይከፍለዋል። የተመረጡትን በደመና ይሠውራል።
ምድርን ፈጠራት ፤ መጠንዋንም አዘጋጀ ፤ ፍጻሜዋንም
እንደምንም ተከተለ ፤ ማዕዘንዋንም አጸና።
ባሕርን ከእናትዋ ሆድ በወጣች ጊዜ በበሮች አነጠራት። 
ልብሷንም ደመና አደረገላት። በጉም ጠቀለላት።
ወሰን አደረገላት። በውስጥዋም መዝጊያዎችንና ቁልፎችን አደረገላት። እስከዚህ ድረሺ ከወሰንሺም አትተላለፊ ፤ ማዕበልሽ በውስጥሽ ይመላለስ (ይነቃነቅ) እንጂ አላት።
በበላይዋ ላይ የንጋት ብርሃን ተዘጋጀ። የአጥቢያ ኮከብም
ትዕዛዙን ዐወቀ። እርሱ ከምድር ጭቃን ነሥቶ ሕያው የሆነውን ፈጠረ። በምድርም ላይ እንዲነጋገር አደረገው።
እርሱ እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ። በጥልቅ ፍለጋም ተመላለሰ።
ከግርማው የተነሣ የሞት ደጆች ይከፈታሉ። የሲኦል በሮችም ባዩት ጊዜ ይደነግጣሉ። ከሰማይ በታች ያለውን ስፋቱን ከሰማይ በላይ የሚሆነውንም እርሱ ያውቃል።
በእርሱ ትእዛዝ ዋግ ከመዝገቡ ይወጣሉ። ከሰማይ በታች ያለ አዜብ(ነፋስ) ይመላለሳል። ዝናምን በምድረ በዳ ያጸናዋል። ሰው በሌለበትና የሰው ልጅ በማይኖርበት ይዘንም ዘንድ።
እርሱ የውኃውን መፍሰሻ ወሰን ፣ ክረምትንም በየዓመቱ
ይከፍታል። በጋውንም ኋላ በጊዜው ያመጣዋል። ደመናውንም በቃሉ ይጠራዋል። ውኃም እየተንቀጠቀጠ ይመልስለታል።
ብልጭልጭታውን እርሱ ይልከዋል ፤ እርሱም ይሄዳል። ምንድር ነው እያለ ይመልስለታል። እርሱ ደመናን በጥበቡ ይቆጥረዋል። 
ሰማይን (ጠፈርን) ወደ ምድር ያዘነብለዋል።
እርሱ ብቻ የአርያምን ኃይል ለበሰ። በምስጋናና በክብር
ተጌጠ።
እሳታውያን ኪሩቤል ፣ ብርሃን የለበሱ ሱራፌልም እርሱን
ያመሰግኑታል። በማያርፍ ቃል ፣ ዝም በማይል ፣ በማይደክምም አንደበት ሁሉም ተባብረው ተሰጥኦ ባለበት ባንድ ቃል የጌትነትህ ምስጋና በሰማይ በምድር የመላ ፍጹም አሸናፊ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ይላሉ።
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ጸባዖት ፍጹም ምሉዕ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ።
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ፍጹም አሸናፊ እግዚአብሔር የጌትነትህ ምስጋና በሰማይ የመላ ነው። 
Holy Holy Holy, perfect Lord of hosts, heaven and earth are full of the Holiness of Thy Glory.
ለሌሎችም ሼር አድርጉት
 
                                         
 
                                                                                                     
                                                                                                     
                                         
   
   
   
   
     
   
   
  