
23/09/2024
- የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ነገር
- ግብፆች ሶማሊያ ገብተዋል። በጣም ብዙ መሣሪያ እያመላለሱ ሲሆን አሜሪካ ደግሞ ለግብፅ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ እርዳታ ለመልቀቅ ወስናለች። ይህ እርዳታ በየአመቱ ይሰጥ የነበረና ታግዶ የቆየ ነው። እርዳታው ግብፅ ለእስራኤል ለምታደርግላት የፖለቲካ ድጋፍ ክፍያ መሆኑ ነው። ግብፅና እስራኤል በፕሬዚዳንት ካርተር አስተባባሪነት በአሜሪካው ካምፕ ዴቪድ በ1978 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የተደረገ ስምምነት አላቸው። ግብፅ ከዛ ስምምነት በኋላ ፍልስጤማውያንን ከድታ የእስራኤልን ሀገርነት ተቀብላ ሌሎች የአረብ ሀገሮች እንዳይረብሹ ታስተባብራለች። ለዚህም በየአመቱ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ እርዳታ ይሠጣታል ከአሜሪካ። ይህ በሌሎች የኢኮኖሚና ድህነት ቅነሣ ዘርፎች አሜሪካ ለግብጽ ከምትሠጠው እርዳታ ውጭ ነው። በአጠቃላይ አሜሪካ ለግብጽ በየአመቱ በአማካይ እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ትደጉማለች።
- የሶማሊያው የውጭጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አከባቢ በሰጡት ቃለመጠይቅ “የኢትዮጵያን መንግስት እየተዋጉ ያሉ የኢትዮጵያ አማጺዎችን ለመርዳት እንፈልጋለን። ከነርሱም ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥሪ እናቀርባለን በራሳቸውም ፍላጎት ከመጡ እናግዛቸዋልን ብለን አስበናል” ብለዋል ባለፈው ሳምንት። ከዚህ ቀደም የዛሬ 15 ቀን ገደማ ኦነግ ሸኔና የሶማሊያው አልሻባብ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ብቻ ሳይሆን እየሰሩም እንደሆነ የኬኒያና የኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተው ነበረ። የሚያስገረመው በጋዜጠኛው “ ከህውሃት ጋር ግንኙነት ጀምራችኋል ወይ?” ተብለው የተጠየቁት ሚኒስትረ “ኢትዮጵያ እንድትበታተን የሶማሊያ መንግስት ፍላጎት አይደለም። መበታተኗም ይጎዳናል።” ሲሉ አስገራሚ መልስ ሰጥተዋል። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ መንግስት በይፋዊ ሁኔታ በአማራ ክልል ከፋኖዎች ጋር፣ በኦሮሚያ ክልል ከኦነግ ሸኔ ጋር ግጭት ውስጥ ይገኛል። በሶማሊ ክልል ይንቀሳቀስ የነበረውና ከፍተኛ አቅም የነበረው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ወደሰላማዊ ትግል ተመልሶ ግጭት ማቆሙ የሚታወስ ነው። በመሆኑም ሶማሊያ ለኢትዮጵያዊ ታጣቂዎች ድጋፍ እሰጣለሁ ካለች አብረዋት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉት ሃይሎች እነዚሁ ሁለት ቡድኖች ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው። የሚያስገርመው ነገር ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነውን ድንበር መቆጣጠር የማትችል ሲሆን ጭርሱን የሶማሊያ መንግስት ከሞቃዲሾ ውጭ ምንም አይነት ተጽዕኖ የሌለው መሆኑ ነው። ምናልባት የሚሰጥ ድጋፍም ካለ በሞቃዲሾ ቢሮዋቸውን እንዲክፍቱ እንዲሁም ከነግብጽ ጋር በይፋ እንዲገናኙ የማገዝ ካልሆነ በቀር ተርፎ የሚሰጥ ገንዘብም፣ የመንቀሳቀሻ ቦታም ሆነ የፖለቲካ አቅም የላትም ሶማሊያ።
- በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዋና ዋና በደቡብ ሶማሊያ የሚገኙ አየር ማረፊያዎችን ተቆጣጥራለች። እነዚህ ወደቦች በደቡብ ሶማሊያ የሚደረጉ ማናቸውንም የወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ያስችላሉ ተብሏል። ግብጽ ከሞቃዲሾ እንዳትወጣ ያደርጋታል የተባለው ይህ ወታደራዊ እርምጃ የተወሰደው ጳጉሜ ውስጥ ነበረ። አየርማረፊያዎቹም **በ[Luuq](https://en.wikipedia.org/wiki/Luuq), [Dolow](https://en.wikipedia.org/wiki/Dolow), [Bardhere](https://en.wikipedia.org/wiki/Bardere)፣ [Garbahare](https://en.wikipedia.org/wiki/Garbahare)፣ Shaati Guduud, Waajid, Doolo,Dinsoor, and Berdaale የሚገኙ ናቸው።** የሶማሊያ መንግስት የሚቆጣጠረው ብቸኛው አየርማረፊያ የሞቃዲሾ የሚገኘው የኤደን አዴ አየርማረፊያ ብቻ መሆኑ ነው።
- በዚህም በደቡብና ምስራቅ ሶማሊያ የሚገኙ ጎሳዎች አልሻባብን የገታችው ኢትዮጵያ ነች ብለው ሶማሊያውያንና የሶማሊያ ክልሎች ድጋፍ እየሠጡ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያወያን በተለይም በደቡባዊ ሶማሊያ ከተሞች በሰላማዊ ሰልፍ ኢትዮጵያን ሲደግፉ ታይተዋል። የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘው የወጡት እነዚህ ሶማሊያውያን የሶማሊያ ፌደራል መንግስት የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ ያሳለፈ ውሳኔ ትክክል አይደለም የግብጽ ወደ ሶማሊያ መምጣትን እንቃወማለን ሲሉ ታይተዋል። ከዚህ ቀደም ኤርትራና ግብጽ ለሶማሊያው አሸባሪ ቡድን አልሻባብ የመሳሪያ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆየተው በኤርትራ ላይ የመሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣልባት ተደርጎ ነበረ። ይህም ማዕቀብ የተነሳው በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥያቄ መሆኑ ይታወሳል። በሌላ በኩል ሁለት የሶማሊያ ክልል አስተዳደሮች የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያን ለቅቀው ይውጡ መባሉን ተቃወመው እንደነበር የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሃይል በተለይም በደቡባዊ የሶማሊያ ክልሎች ማለትም በጁባላንድና ሳውዝ ዌስት ስቴት የሚገኙ ሲሆን በአከባቢው የጎሳ መሪዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ነዋሪዎች ተቅባይነት አላቸው።
- ቱርክ በሶማሊያ ተመዘግዛጊ የረጅም ርቀት ሚሣኤሎችንና የህዋ ሮኬቶችን መሞከሪያ ጣቢያ ልታቋቁም ከሶማሊያ ጋር እየተደራደረች ነው። ቱርክ ከሃገሯ ሆና በትንሹ ከ1000 ኪሎሜትር ያላነሰ ርቀት የሚመዘገዘጉ ሚሳኤሎችንና የጠፈር ሮኬቶችን ለመሞከር አትችልም። ቱርክ በሃገራት በተጣበበው የትንሿ ኤሺያ አከባቢ እንደመገኘቷ እንደፈለገች ሚሳኤል እየተኮሰች የሚወድቅበትን ማወቅ አትችልም። ለዚህም ከሶማሊያ ጋር ከተስማማች ወደ ደቡብ ምስራቅ ህንድ ውቅያኖስ በመተኮስ ሙከራ ማድረግ ትችላለች። ከዚህም ሌላ ከሶማሊያ ጋር ለ10 ዓመታት የሚቆይ የሶማሊያን የባህር ድንበር የመጠበቅ ስምምነት የዛሬ 15 ቀን አከባቢ ተጀመሯል። ቱርክ ይህንን አገልግሎት በመስጠቷ ሶማሊያ ከውቅያኖስ ድንበሯ የምታገኘውን ገቢ 30 በመቶ ተካፈላለች። ይህ በእንዲህ እንዳለም ቱርክ በሶማሊያ የውቅያኖስ ድንበር አከባቢ ነዳጅ ለመፈለግ ባገኘችው ፈቃድ መሰረት የነዳጅ ፈላጊ መርከብ አሰማርታለች። ይህንንም መርከብ ለመጠበቅ ሁለት አነስተኛ የጦር መርከቦችን እንደምታሰማራ ተናገራለች። ይህም ወደ ደቡብ ወደ ህንድ ውቅያኖስ የሚተኮሱ ይሆናሉ። ቱርክ የሶማሊያን ድንበር መጠበቅ፣ እንደገና ሶማሊያን እና ኢትዮጵያን ከማደራደር ሚናዋ ባለፈ አሁን ደግሞ የሚሳኤል መሞከሪያ ጣቢያ ልታድርጋት ነው። የሚገርመው የቱርክ ነገር ከቅኝ ግዛት መለስ የሚለው ራሷ ሶማሊያ እንዲህ እንድታደርግ በመጋበዟ ብቻ ነው።
- ሶማሊላንድ የግብፅ የባህል ቋሚ ኢግዚቢሽን እንዲዘጋ ወስናለች። ግብጻውያን ሠራተኞቹም በ72 ሠዓታት ከሀገሪቷ ተባረዋል። ግብጽ በሶማሊላንድ ይህን ያክል ተወላጆቿ ኖረው የባህል ማዕከል ባያስፈልጋትም ማዕከሉን ከፍታ ለረጅም ጊዜ ስትጠቀምበት ቆይታለች። ከሶማሊያ ጋር የመከላከያ ስምምነት የተፈራረመቸው ግብጽ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ሶማሊላንድ መጉዳቷ የሚቀር አይደለም። ደሞ የሚገርመው የግብጽ የባህል ማዕከል የሚገኘው ከሶማሊላንዱ ፕሬዝዴንሺያል ቤተመንግስት አጠገቡ መሆኑ ነው። ሶማሊላንዳውያኑ የግብጽ የባህል ማዕከል ሰራተኞች በስውር የስለላ ስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው ከሃገሬ ይውጡልኝ ብላ አስወጥታቸዋለች።
- የጅቡቲ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ የታጁራን ወደብ የማስተዳደርና ኢትዮጵያ በዛ ወደብ የመጠቀም ሙሉ መብት እንሰጣታለን ብለዋሉ። በርግጥ ኋላ ላይ ቆየት ብለው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ሳይሆን በጋራ እናስተድረው ነው ያልነው ብለዋል። ወጣም ወረደ ቀዝቃዛ ውሃዋንና የሃገሪቷን 85% የሚሆን ገቢ ከኢትዮጵያ የምትለፈው ጂቡቲ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በፓርላማ ቀርበው ወደብ ያስፈልገናል ሲሉ የምንሰጣችሁ ወደብ የለንም ስትል ነበር። በመስታወት ቤት ያለ ቀድሞ ድንጋይ አይወረውርም እንደሚባለው ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ እንዳቀዱት ከሆነላቸው የመጀመሪያ የንግድ ተጎጂ ራሷ ጀቡቲ ትሆናለች። በርግጥም ከመንግስት ድክመት ይሁን ከሌላ ባይታወቅም ኢትዮጵያ ጅቡቲ ላይ 90% የሚሆን የገቢ / ወጪ ንግዷን ማሳረፏ የሚገርም ነው። ኢትዮጵያ በዙሪያዋ የሱዳን ፖርት ሱዳን፣ የኤርትራ አሰብና ምጽዋ፣ የሶማሊላንድ ዘይላ፣ የኬኒያ ሞምባሳና የላሙ ኮሪደር ከበቂ በላይ የወደብ አማራጮች ቢሰጣትም ከጅቡቲ ተጣብቃ ራሷን ቅርቃር ከታለች። በዚህ ምክኛትም ጅቡቲያውያኑ ለኢትዮጵያወያን ያላቸው የወረደ ግምት በጣም የሚገርም ነው። ይህንንም የጅቡቲ ተመላላሽ ሾፌሮች የሚያረጋግጡት እውነት ነው።
- የግብፅ የደህንነት ባለስልጣናትና ሌሎች ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ የተላከ መልዕክት ለፕሬዚዳንት ኢሣይያስ አፈወርቂ አድርሰዋል። ግብጽ በህዳሴ ግድብ ምክኛት አናቷን እንደተመታች ድመት በምስራቅ አፍሪካ እየተንደፋደፈች ትገኛለች። ከዚህ ቀድም በሶማሊያ የነበራቸውን መናበብ ሊደግሙት እየተንደረደሩም ይገኛሉ። እንደተለመደው ግብጽ የጦርመሳሪያና ገንዘብ ለአልሻባብ ለማድረስ ኤርትራን ለመጠቅም ያሰብች ይመስላል። በርግጥ የአሁኑን ሁኔታ ለየት የሚያደርግው ግብጽ በቀጥታ በሶማሊያ ወታደሮቿን ለማሰማራት እንድል ማግኘቷ ነው። በዛው ሳምንትም የኢትዮጵያ አየርመንገድ የኤርትራ በረራውን አቋርጧል። ኤርትራ እንደተለመደችው በኤርትራ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት አፍና ይዛለች። ከዚህ ቀደም በነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግጭት በተጀመረበት ወቅትም በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚያወጡ ኢምፖርትና ኤክስፖርት እየተደረጉ የነበሩ ምርቶችን አፍና መውረሷ የሚታወስ ነው። ይህ እንግዲህ በኤርትራ ኗሪ ኢትዮጵያውያን የተወረሰውን አይጨምርም።
- የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ደግሞ ከሞሮኮ መንግስት ጋር ስብሰባ አካኼደው የተለያዩ የወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ኝኙነቶች ላይ ስምምነት ፈጸመዋል። ይህ የሆነው ባለፈው ወር ነበር። ሞሮኮ ብድሬዳዋ አከባቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚወጣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተስማምታለች። ይህንን ያነሳንበት ምክንያት ድንገተኛው የኢትዮጰያና የሞሮኮ ፍቅር ከምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ትኩሳት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንዳለ በመጠርጠር ነው። ሞሮኮ ከታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ጠላት ጋር ዘመናትን የተሻገረ መልካም ወዳጅነት ይኑራት እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመግባባቶች እየታዩ ይገኛሉ። ሞሮኮን ለረጅም ጊዜ የሚያቆስላት በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እውቅና የተሰጠውና ከሞሮኮ ተገንጥሎ ሃገር ለመሆን የሚዋጋ ተገንጣይ ቡድን አለ። ሞሮኮ ኢትዮጵያ ለዚህ ቡድን የሰጠችውን እውቅና እንድታነሳ ትፈልጋለች። ኢትዮጵያም ሞሮኮ ከግብጽ ጋር ያላትን ወዳጅነት ቀንሳ በአባይ ጉዳይ ኢትዮጵያን እንድትደግፍ ትፈለጋለች። ወቅቱ ደሞ በሞሮኮና ግብጽ መካከል በግልጽ የሚታይ ጽብ የተነሳበት መሆኑ ሞሮኮ የኢትዮጵያን ድጋፍ አጥብቃ ትፈልጋለች።