
21/03/2022
የኦሮሚያ ክልል ለሰላም፥ለመልካም አስተዳደርና ለልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስትና ህዝብ የሀገር ሉዓላዊነት እና ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የልማት ስራዎችን ለማፋጠን በልዩ ትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፋት ሰባት ወራት የተከናወኑ የክልሉን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት፥ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ በማቅረብ ላይ ናቸው።
ሽብርተኞቹ የሸኔ፣ አባ ቶርቤ እና የህወሓት ቡድን አባላት ክልሉን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እና የልማት ስራዎችን ወደ ኋላ ለመመለስ ያደረጉትን ያልተቋረጠ እንቅስቃሴ ለመመከት መሰራቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
አሁንም እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች በክልሉ የተለያዩ ዞኖች እየፈጸሙ ያሉትን ከፍተኛ ውድመት መከላከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት።
የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍ የ6 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል እህል፤ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ፍራፍሬ:፤ የ3 ነጥብ 26 ሚሊየን የቁም እንስሳት የገበያ ትስስር መፈጠሩን አንስተዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኦሮ ፍሬሽ ኢኒሼቲቭም ሰፊ የገበያ ትስስር እየተፈጠረበት መሆኑን ተናግረዋል።
በ2013/14 ዓ.ም የምርት ዘመን በክረምት እርሻ ልማት ከ6 ሺህ 309 ሄክታር መሬት 188 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት ስለመገኘቱ በሪፖርቱ ጠቅሰዋል።
በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በዘንድሮው ዓመት ከ350 ሺህ ሄክታር 17 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንና በአንደኛው ዙር ልማት ከ355 ነጥብ 1 ሄክታር ማልማት መቻሉንም ነው የተናገሩት።
ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማትም 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኝ ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን የ2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዝግጅት ስራ መጠናቀቁንም ርእሰ መስተዳደሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!