06/11/2025
ባንኮች በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ቅርንጫፍ መክፈት ስለሚችሉበት ሁኔታ የሚደነግግ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚፈልጉ ባንኮች፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚገኙ ባንኮች ካላቸው ጠቅላላ ሀብት፣ በመጨረሻው የበጀት ዓመታቸው ሪፖርት መሠረት ቢያንስ ሁለት በመቶ የሀብት ድርሻ እንደሚይዙ ማሳየት የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸው የሚደነግግ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ፡፡
ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ሥራ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር በተመለከተ፣ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ቅርንጫፍ የሚከፍቱ ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን፣ የቁጥጥር ሒደትና የባንኮቹን የሥራ እንቅስቃሴ ለመደንገግ አዲስ ረቂቅ መመርያ ማዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡
ብሔራዊ ባንክ ባወጣው ሪፖርት (Financial Stability Report, November 2024) መሠረት፣ እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ የተመዘገበ የባንኮች ጠቅላላ ሀብት 3.3 ትሪየን ብር መድረሱን ያሳያል፡፡
ረቂቅ መመሪያው በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖቹ ቅርንጫፍ የሚከፍቱ ባንኮች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን የጠቅላላ ሀብት መጠን፣ የካፒታል ብቃት ምጣኔ (Capital Adequacy Ratio)፣ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ምጣኔ (Liquidity ratio)፣ እንዲሁም የተበላሸ ብድር ምጣኔን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ተካተውበታል።
ከድንጋጌዎቹ መካከል በዞኖቹ ቅርንጫፍ የሚከፍቱ ባንኮች ፈቃድ ለማግኘት ከሚያመለከቱበት ጊዜ ጀምሮ ወደኋላ ባሉት አራት ተከታታይ የበጀት ሩብ ዓመቶች ሪፖርት መሠረት፣ ከተጣራ የወጪና ዕዳ ኃላፊነት (net current liabilities) ላይ እንዲያስመዘግቡ በብሔራዊ ባንክ ከሚገደዱት የ15 በመቶ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት ምጣኔ ተጨማሪ ሦስት በመቶ ከፍ ሊያደርጉ ይገባቸዋል ተብሏል፡፡
እንዲሁም የተበላሸ የብድር መጠናቸውም ከአምስት በመቶ ከፍ ሊል እንደማይገባው የተደነገገ ሲሆን፣ ቅርንጫፍ የሚከፍቱ ባንኮች በኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለሚንቀሳቀስ የትኛውም ግለሰብ ሆነ የንግድ አካላት፣ ሁሉንም የባንክ አገልግሎቶቻቸውን ማቅረብ የሚችሉ ሊሆኑ እንደሚገባቸውም በረቂቁ ተደንግጓል፡፡
በረቂቅ መመርያው ማንኛውም ባንክ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመሥራት የግዴታ የብሔራዊ ባንክ ፈቃድ እንደሚያስፈልገው የተገለጸ ሲሆን፣ በዞኖቹ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ያለው የትኛውም ባንክ የሚከፍተው ቅርንጫፍ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ማረጋገጥ ይገባዋል ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ቅርንጫፎች ከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባንኮች፣ ረቂቅ መመርያው ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ በሚኖር አንድ ዓመት ውስጥ፣ በረቂቁ ውስጥ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ