
12/08/2025
ተመድ ጥልቅ ማሻሻያ ያስፈልገዋል - ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶሃን
******************
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግዳጁን በትክክል ለመወጣት ጥልቅ ማሻሻያ ያስፈልገዋል ሲሉ የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን የተመድ 80ኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተጣለበትን አደራ መወጣት እንዲችል ከፍተኛ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ግልፅ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም አቀፋዊ ፍትህን የሚወክል መድረክ እንዲሆን ለማድረግ የጋራ ሀላፊነት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
ከ80 ዓመታት በፊት ለዚህ ድርጅት መሠረት የጣሉት መስራቾች ባሳዩት ቁርጠኝነት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በማጠናከር ዓለም አቀፋዊ ሰላም፣ ብልጽግና፣ የጋራ መተማመን እና መተሳሰብ ዳግም እንዲሰፍን እና ወደ ፊትም እንዲቀጥል ለማድረግ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የበለጠ ውጤታማ፣ ቀልጣፋ እና በፋይናንስ አቅሙ ጠንካራ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሀገራቸው በንቃት ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እንደ ሰው ልጆች ተስፋ የሚመለከቱ አባል ሀገራት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስባለሁ ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል።
በፈረንጆቹ 2025 የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት እያከበረ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ታሪካዊ የሚሆነውን 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጪው መስከረም የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ABM WORLD ኤቢኤም ወርልድ