26/12/2024
ተሻሻለ ተብሎ ወዲያው ግን ወደባሰ ሁኔታ ውስጥ የገባው የሀዋሳ የቤንዚን እጥረት
(መሠረት ሚድያ)- በሀዋሳ ከተማ ቤንዚን ከጠፋ በርካታ ሳምንታት ማስቆጠሩ ይታወቃል፣ ይሁንና ከሰሞኑ መስተካከል እንዳሳየ ተዘግቦ ነበር።
ከሰሞኑ ደግሞ ችግሮ ተመልሶ ወደነበረበት ብቻ ሳይሆን ወደባሰ ሆኔታ ውስጥ መግባቱን መሠረት ሚድያ ሰምቷል።
"ቤንዚን ለመቅዳት ህዝቡ ከሌሊቱ 10:30 ጀምሮ ነው የሚሰለፈው፣ ነገር ግን ተሰልፎም የማይቀዳበት ሁኔታዎች በብዙ ይስተዋላሉ" የሚሉት ለሚድያችን ጥቆማቸውን የሰጡት ነዋሪዎች የከተማው የመንግስት ቢሮዎች እና አመራሮች አሁንም ከማደያዎችና ከጥቂት ግለሰቦች ጋር የጥቅም ጉዳይ መኖሩን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዋሳ የተሰራውን የኮሪደር ልማት ለማስመረቅ ይመጣሉ ተብሎ በዕለቱ ከሌሊቱ 10:00 ሰዓት ጀምሮ ቤንዚን ለመቅዳት የተሰለፉ ሰዎችን ጠዋት 4:00 ሰዓት አካባቢ ፖሊስ "ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስለሚመጣ ተበተኑ" ብሎ በፈጠረው ግብግብ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
"ፖሊስ ወጣቶችን በፓትሮል ሲበትን በጠዋት ተነስተው በራቸው ላይ ስፖርት እየሰሩ የነበሩ ልጆች ተገጭተዋል፣ ከባድ የሚባል የአካል ጉዳትም የደረሰባቸው አሉ" ያሉት ነዋሪዎች ጉዳዩ ከምሬትም በላይ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ነዳጅ የሚቀዳባቸውን ማደያዎችና ምደባ በቴሌግራም ቻናል ያሳውቃል።
"ቤንዚን ለመቅዳት ሁሉም ከለሊት 10:00 ጀምሮ በየማደያው ይሰለፋል፣ ግን ቴሌግራም ላይ ሲለቀቅ ሁሉም ቤንዚን ወደአለበት ወደ ተመደበበት ማደያ በሚያደርገው እሽቅድድም ባጃጆች እተገለበጡ እየተጋጩ ነው፣ ሰው ከሞተር ላይ እየወደቀ እየተጎዳ ነው የቤት መኪኖች እተጋጩ ነው" ብለው ምሬታቸውን አቅርበዋል።
"በዛ ላይ በሌሊት 10:00 ሰዓት ላይ ወጥተህ በግምት ማደያ አካባቢ ስትቆም 'አስፓልቱን ልቀቅ' ተብለህ በፖሊስ ትደበደባለህ፣ በዛ ብርድ በዱላ ነው የሚመቱህ። በሀዋሳ ከተማ ከቤንዚን ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ነው" በማለት ሁኔታውን ለመሠረት ሚድያ አስረድተዋል።
መረጃን ከመሠረት!