
01/10/2025
ኢሬቻ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው ገዳ ስርዓት አንዱ እሴት የሆነው ኢሬቻ የሰላምና የምስጋና በዓል ነው።
በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበትና የሚፈልገውን ፈጣሪ እንዲፈጽምለት የሚጠይቅበት ነው:: ኢሬቻ በሁለት የተለያዩ ጊዜ እና ስፍራ ይከበራል። አንዱ ኢሬቻ መልካ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ኢሬቻ ቱሉ ነው።
የጭለማ፣ ጭጋጋማ እና ከባዱ የክረምት ወቅት አልፎ ወንዞች ጎድለው የውሃ ሙላት ካለፈ በኋላ መሬቱ ጠገግ ሲል የሚከበረው ኢሬቻ መልካ ክረምት እና የውሃ ሙላት የለያያቸው ሰዎች መገናኘት የሚጀምሩበት ነው፡፡
ክረምቱን በእርሻ ስራ የደከመ ሰው የሚያርፍበት እና የላቡን ተስፋ በሰብሉ ማበብ ማየት በሚጀምርበት ወቅት የሚከበረው ኢሬቻ መልካ በመስከረም ወር መጨረሻ ውሃ በሚገኝበት ስፍራ ሲከበር ለፈጣሪ ምስጋና ይቀርባል።
ኢሬቻ ቱሉ ዝናብ ሲርቅ፣ ወንዞች ሲደርቁ፣ መሬት ለከብቶች ሳር ስትነሳ፣ ድርቅ እና ረሃብ በሰውና በእንስሳት ላይ ሲያይል ዝናብ እንዲጥል ወደ ተራራ በመውጣት ለፈጣሪ ልመና የሚቀርብበት ነው።