07/09/2025
የአባት ፍቅር
ህልመኛው ሰውዬ/The Visionary
አንድ ጎልመስ ያለ አባት ሴት ልጁን እጇን ይዞ ቦሌ ዓለም አቀፍ የበረራ ጣቢያ እየጎተተ ይገባል።
ልጅቷም እያለቀሰች መሄድ አልፈልግም እያለች በአቅሟ ወደ ኋላ ትጎትታለች።
እስኪሳፈሩ ድረስ ለተወሰነ ደቂቃ የአየር ጣቢያዉን ልጅቷ እያለቀሰች ስታምሰው ከቆየች በኋላ በረራው ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ከሆነው አየር ገቡ።
በአየሩም ዉስጥ ገብተው ልጅቱ ማልቀሷን አላቆመችም ነበር። ከዛም አየሩ በረራዉን ጀምሮ ሰማይ ላይ ተረጋግቶ መሄድ ሲጀምር አባት "በድሮ ጊዜ አንዲት ጥበበኛ ንግሥትና አንድ ችኩል ንጉሥ ነበሩ" አለ።
ልጅቱም ማልቀሷን ትንሽ ቀነስ አድርጋ ማድመጥ ጀመረች። አባትም በሚያምር አተራረክ መተረኩን ቀጠለ። "እጅግም የሚዋደዱ ነበሩ። ታዲያ አንድ ቀን ሁለት ባላገሮች ተጣልተው ወደ ንጉሡ የፍርድ ሸንጎ ይቀርባሉ።
ጠባቸዉም ምንድን ነው አንድ ሕጻን ጥጃ የኔ ነው የኔ በሚል ነበር።
አንደኛው ገበሬ ፈረስ ሌላኛው ደግሞ ላም ነበራቸው። እና ሁለቱም በአንድ ጋጥ (የከብት ማሳደሪያ ቤት) ይጠቀሙ ነበር። ታዲያ ከዕለታት በአንድ ቀን ጠዋት ተነስተው ወደ ጋጡ ሲመጡ የተጣሉበት ሕጻን ጥጃ ከፈረሱ ስር ተኝቶ ያገኙታል።
ታዲያ ባለፈረሱ ሚደንቅ ነው ፈረሴ ጥጃ ወለደልኝ ሲል ባለላሟ ደግሞ ከመቸ ወዲህ ነው ፈረስ ጥጃ ሚወልደው ላሜ ከወለደችው በኋላ ወዳንተ መተ ነው እንጂ፤ የኔ ላም ነው የወለደችው እና የኔ ነው ተባብለው ተጣልተው ገንጉሡ ዘንድ መጡ።"
አባትም ልጁ ዝም ስትል እየሰማች ነው አይደለም ብሎ ለማረጋገጥ ዝም ሲል ቀና ብላ አየችው።
አባትም ደስ ብሎት መተረኩን ቀጠለ "ታዲያ ችኩሉ ንጉሥ ጥጃው ከፈረሱ ስር ከተገኘ ያንተ ነው ማለት ነው ብሎ ለባለፈረሱ ይፈርዳል። ከዛም ባለላሟ ባለቤት ግራ ገብቶት ሳለ ለንጉሡ ሚስት ጉዳዩን ቢያስረዳ መፍትሄ እንደሚያገኝ ሰማና ከብዙ ልፋት በኋላ አግኝቶ ጉዳዩን ካስረዳት በኋላ ንግሥቲቱ እንዲህ አለችው "ነገ ከከተማ ይወጣል ታዲያ ንጉሡ በመንገድ ሲያልፍ የአሳ መረብ እንደሚጥል መስለህ በባዶ መሬት ላይ አስመስል ያኔ አይቶ ምን እያደረግህ ነው? ሲልህ ፈረስ ጥጃ ከወለደ ደረቅ መሬት አሳ ያበቅላል ብዩ ነው በለው ታዲያ እንደነገርኩህ እንዳትነግረው አለችው።
ገበሬዉም ንግሥቲቱ እንዳለችው አደረገ ከዛ የፈረደው ፍርድ ትክክል እንዳልነበር ተረዳ፤ ሆኖም ግን በአንድ ገበሬ በመበለጡ ተናዶ ይህን ዘዴ ሰው ነግሮህ ይሆናል እንጂ አንተ አታመነጨዉም ብሎ ማን እንደመከረው እንዲነገረው አፋጠጠው፡፡
ገበሬዉም ላለመናገር ቢሞክርም ዱላ ሊመጣበት መሆኑን ሲያይ ፈርቶ ምስቱ እንደሆነች ተናገረ።
በዚህም ሚስቴ በአንድ ገበሬ እንድዋረድ አድርገኛለች ብሎ በመናደድ "ነገ ጠዋት ከዚህ ሁሉ ምትወጅዉን አንድ ነገር ብቻ ይዘሽ ወጥተሽ ትሄጃለሽ" አላት ንግሥቲቱም ቢከፋትም ሳታጉረመርም እሺ ብላ "እንዲያው ንጉሥ ሆይ ካላስቸገርኩህ ዛሬ ለየት ያለ ድግስ እንዳደርግ ቢፈቅዱልኝ" አለች።
ደስ እንዳለሽ ብሎ ፈቀደላት። እሷም ከወይን ጠጅ የሚያሰክር አዘጋጅታ በቤት ሁሉ ያለዉን ጋበዘች። ታዲያ ሁሉም ሰከሩና ንጉሡም ጭምር ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ተኙ ንግሥቲቱም ንጉሷን በነጭ ልብስ ጠቅልላ ይዛው ወደ ምታርፍበት ቤት ወሰደችው። ጠዋትም ሲነጋ ንግሥቲቷ ከዉጭ ሥራ እየሠራች ሳለ ንጉሡ ተነስቶ "የት ነኝ? ማነው ከዚህ ያመጣኝ?" እያለ ሲጮህ ሰምታ ወደሱ መጣች። ንግሥቲቱም "ተረጋጋ ከኔ ጋር ነህ" ትለዋለች።
"ከኔ እንድትርቂ አልነገርኩሽም ደግሞ ማነው ከዚህ ያመጣኝ" አላት። እሷም "እኔ ነኝ የምትወጅዉን አንድ ነገር ብቻ ዉሰጅ ብለህ ቃል አልገባህልኝም?" ብላ ስትጠይቀው አዎ ቃል ገብቼልሻለሁ ታዲያ ከኔ ጋር ምን ያገናኘዋል? አላት አየህ እኔ ከዚያ ቤት አንድ የምወደው ነገር አንተን ብቻ ነው ለዛ ነው ያመጣሁህ አለችው፡፡ ንጉሥም እየተጸጸተ ይቅርታ ንግሥቴ ሲጀመር ስህተቴን አረምሽኝ እንጂ አንቺ ምንም አላጠፋሽም ብሎ ታረቁ፡፡
በፍቅርም እስከ ዕለተ ሞታቸው አብረው ኖሩ።" ብሎ ለሕጻኗ ነገራት።
"አየሽ ልጄ እኔም ምንም ነገር እንዳይጎዳሽ ስለምፈራና እኔ አንቺን ስለምወድሽ ነው ከኔ ጋር እንድትሆኝ የምወስድሽ ደሞ ቃል እገባልሻለሁ አንቺን ለማሳደግ ሚስት የሚባል አላገባም ማንም አንቺን እንዲያይብኝ አልፈልግም አላት ልጅቷም በፍቅር አቅፈችው ተቃቀፉ።
"አየሽ ልጄ እኔም ስለምወድሽ ምንም ነገር እንዳይጎዳሽ እጠነቀቅልሻለሁ፤ ሁሌም የሚሆንሽን እና የሚጠቅምሽን ነገር ብቻ አደርግልሻለሁና፤ አይዞሽ በዘመኔ ሁሉ እስካለሁ ድረስ ኃላፊነቴን እወጣለሁ፡፡" አላት፡፡