
27/09/2025
1. የሰው ልጆች በመጀመሪያ በውልደት ወደዚህ አለም ሲመጡ የመጀመሪያው አንድ ደቂቃ ከሚቀጥሉት አርባ አመታት በላይ የበለጠ ፋይዳ አለው። ምክንያቱም የመጀመሪያው አንድ ደቂቃ ከመሞት በፊት ያለው ትልቁ የህይወት ለውጥ ነው።
2. ፍርሃት የፈሪም የጀግናም መነሻ ነው። ፍርሃት ለፈሪ ጭንቀቱ ሲሆን፤ ለጀግና ደግሞ ጀብዱው ነው።
3. መማር ባለሙያ ያደርጋል፤ መኖር ደግሞ አዋቂ ያደርጋል።
4. ሰው የሆነውን የሚሆነው በአጋጣሚ አይደለም።አዋቂው ሰው ህፃኑ ልጅ በልጅ አዕምሮው የፃፈውን ተውኔት የሚተውን ተዋናይ ነው። የልጅ ጭንቅላት የተባለውን ይይዛል፤ አዋቂ ደግሞ የያዘውን ይተገብራል። አዋቂው ሲያለቅስ ወይም ሲያዝን እንደህፃን አባብይው።
5. ተስፋ የመኖር ምክንያት ነው።ሰውን እንዲኖር የሚያደርገው መለወጥ አለመለወጡ ሳይሆን የመለወጥ ተስፋው ነው። ቢሆንም ግን ህይወት ተከታታይ መሆኗን መገንዘብ ይጠቅማል። ዛሬ የምንኖረው በትላንት ምክንያት ነው።
6. ሰው መሆን ማለት ራቁታችንን ከተወለድን በኋላ፤ ከልብስ ጀምሮ አካላችንን ከሚሸፍኑት ሽፋኖች መላቀቅ ነው። ሰው ሰውነቱን የሚያጣው ራቁቱን ከእናቱ ማህፀን ሰው ሆኖ ተወልዶ በማህበረሰብ፣ በልብስ፣ በትምህርት፣ ሃይማኖት፣ በብሔር የመሰሉ ግዑዛን አልባሳትን በመደረብ ነው።
7. እውነተኛ ለውጥ የማይኖረው ሰው ስላልጣረና ስላልሞከረ ሳይሆን ለውጥ ሂደት እንጂ መድረሻ ስላልሆነ ነው።
8. ጎዳና ላይ የሚያድር ሰው ብርዱን ይለምዳል፣ ፀሃዩን ይታገሳል፣ አውሬ ያስለምዳል፤ ሰውን ግን ይፈራል። ቀኑን ሙሉ ብርድ ሳንፈራ ደረታችንን ገልጠን ራቁታችንን የምንውል ሰዎች፤ ልክ ሲመሽ የውጪ በር ቆልፈን፣ከዛ የሳሎን በር ቆልፈን፣ የጓዳ በር ቆልፈን፣ አልጋችን ውስጥ ገብተን ብርድልብስ ለብሰን፣ ብርድ ልብሱ እንዳይኮሰኩሰን አንሶላ ደርበን፣ አንሶላው እንዳይቀዘቅዘን የለሊት ልብስ ለብሰን ...በነዚህ ነገሮች ሁሉ ተከልለን እንተኛለን። ይህን እንዲሆን ደግሞ ያደረገው ፍርሃታችን ነው።
9. በታሪክ ውስጥ ትልቁ አምባገነን ታሪክ ራሱ ነው።ሁላችንም የታሪክ ተገዢዎች ነን።
10. የማታሸንፈውን ሰው ተጠያቂ ማድረግ የፈሪነት መፍትሔ ነው።
11. እውነት እኮ የጊዜና የቦታ ድምር ውጤት ነው። የራስን ሃሳብ ሌላው እንዲገባው ማድረግ ማለት ፤ የራሱን ሃሳብ ድንበር አልፈን የሃሳብና አስተሳሰብ ወረራ አካሄድን ማለት ነው።
12. የሚጠፋ ነገር ዐይንህ ስር ተቀምጦ ያለማየትን የመሰለ ዕውርነት የለም። አንዳንዴ ከሞት በኋላ ስለሚኖር መኖር እየጓጓን የውሸት ማመን የለብንም። ስለፀሎታችንን ምንነት በአንክሮ መፈተሽ ያስፈልጋል
13. ሰው የምታውቀው ፍጡር አይደለም። ሁልጊዜ ሰውን የምናውቀው ይመስለናል። እኔ ሐኪም ስከሆንኩና የአንድ ሰው አካል ቀድጄ ልቡን ስላየሁት ሰውን ያወኩት ይመስለኛል። ነገር ግን ሰው በየትኛውም ደረጃ የሚታወቅ ፍጡር አይደለም።
በደረቁ ሳይንስ አጥንተህ ሰው ውስጥ ያለውን ፕሮቲን እንዴት እንደሚሰራ ስላወቅህ ሰውን አውቃለሁ ማለት አይቻልም።
የመማር አንደኛው ችግር (በተለይ እኛ ሐገር) ቶሎ መታበይና የምናውቀው እውቀት እኛ ያመጣነው ሳይሆን ቀድሞ በሌሎች የተፈጠረ መሆኑን የመርሳት ችግር አለብን። እኛ ያወቅነው ከእኛ በፊት የመጡት የፈጠሩትን ነው። ይህንን እንረሳና እኔ ተምሬ ሳውቅ ራሴን አዋቂና ሐሳቡን እኔ የፈጠርኩት የመምሰል ችግር አለብን።
14. እያወቅክ ስትሔድ ትልቅልነትህን ሳይሆን ትንሽነትህን ነው የምትረዳው "
ብዙ ነገር ለመማር መሞከር እይታህን ያሰፋል። የእይታህ አድማስ ሲሰፋ ደግሞ አንተ እያነስክ ነው የምትሄደው። ሰፊ ከሆነው ዓለም ውስጥ አንተ ምን ያህል ኢምንት እንደሆንክ ትረዳለህ። እያወቅክ ስትሄድ ትልቅነትህን ሳይሆን ትንሽነትህን ነው የምትረዳው።
የህይወት ፍልስፍና
የትኞቹን ሃሳቦች ወደዳችኋቸው? አድርጉልን