01/03/2021
የዓረና ፓርቲ መግለጫ ፦
ዛሬ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት- ዓረና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ከዚህ ቀደም በትግራይ እና በፌዴራል መንግስት መካከል የነበረው ፍጥጫ በድርድር መፈታት እንዳለበት ሲያሳስብ መቆየቱን አስታውሷል።
ዓረና ሃሳቤ ሰሚ አጥቶ በትግራይ ከማዕከላይ መንግስቱና ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ውጭ ምርጫ ሲካሄድ የጦርነቱ ጅማሬ ዋዜማ እንደነበር ተገንዝቤያለሁ ብሏል።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሲፈፀም የተፈራው ደርሶ የእልቂት አስከፊ ጦርነት ይፋ ሆነ ፤ ወደ ጦርነቱ ሲገባ ህዝቡ ተነጋግሮበት እና መክሮበት የተደረገ አልነበረም፤ እንኳንስ ህዝቡ የትግራይ ክልል ምክር ቤትም ሳይመክርበት የተካሄደ ነበር ሲል ዓረና ፓርቲ ሁኔታውን አስታውሷል።
ዓረና ፓርቲ ፥ ጦርነት ያህል የሚሊዮኖችን ህይወት የሚያናጋ አጥፊ ተግባር በተወሰኑ የፓርቲ አመራሮች እና ሊሂቃን ሲወሰን ጦሱ በንፁሃን ዜጎች ላይ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነበር ብሏል።
ዓረና በትግራይ በአጭር ጊዜ በየመን፣ በሶርያ፣ ሊቢያ እና ኢራቅ የተከሰተው ዓይነት ውድመት ደርሷል ሲል ገልጿል።
ዓረና ፥ አሁንም በትግራይ የፀጥታ ስጋት፣ በየአካባቢው ተኩስ እና ግድያ አለ ያለ ሲሆን በተለይ በውጊያ ሂደት እና ከውጊያ ውጭ በንፁሃን ወገኖች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ አሁንም ድረስ ቀጥሏል ብሏል።
ይህ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀለት ውድመቱ አሁን ካለው የከፋ ሊሆን ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
ዓረና ፓርቲ አሁንም የትግራይን ህዝብ እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ ምክንያቶችን የዘረዘረ ሲሆን መፍትሄ ያላቸውን ሃሳቦችም ባወጣው መግለጫ ላይ በዝርዝር አስቀምጧል።