
11/08/2025
እውቋ ዓለም አቀፍ የፊልም ተዋናይ
አንጀሊና ጆሊ ኢትዮጵያ ነች
አንጀሊና ጆሊ የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታልን ጎበኙ
ዝነኛዋ አሜሪካዊት ተዋናይት ፣ የፊልም ባለሙያ እና የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ የሆኑት አንጀሊና ጆሊ በዛሬው ዕለት የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።
ተዋናይቷ ያደረጉት ጉብኝት በዋነኝነት ሆስፒታሉ እየሰጠ በሚገኘው መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ (ኤም.ዲ.አር ቲቢ) ህክምና ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ፣ የሚታዩ ለውጦችን እንዲሁም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር።
በጉብኝቱ ላይ አንጀሊና የሆስፒታሉን የቲቢና መድሃኒቱን የተላመደ ቲቢ (ኤም.ዲ.አር ቲቢ) ህክምና አገልግሎት መስጫ ዋርድ ፣ ላብራቶሪ እንዲሁም ታካሚዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አንጀሊና ወደ ሆስፒታሉ ከረጅም ጊዜያት በፊት መጥተው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን በአሁኑ ጉብኝታቸው ላይ ሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ ለውጦች አምጥቶ በመመልከታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አክለውም ሆስፒታሉ ድጋፍ ቢደረግለት በቀጣይ የተሻለ
አገልግሎት ለታካሚዎች መስጠት በሚያስችለው አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዳለ በጉብኝቱ ላይ መገንዘባቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በሆስፒታሉ በቲቢ ህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተገኘው እድገት በእጅጉ የሚደነቅ እና የሚያስተማምን ስለሆነ በቀጣይ በጂ.ኤች.ሲ (Global Health Committee (GHC)) በኩል ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብርሃም እሸቱ በበኩላቸው ቲቢን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ተዋናይቱ ላሳዩት ዘላቂ ቁርጠኝነት ፣ ልግስና እና በቀጣይ ለሚያደርጉት ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አንጀሊና ጆሊ ከፊልም ስራ ባሻገር በአለምዓቀፍ ደረጃ ለስደተኞች እና ለሰብአዊ መብቶች ጥብቅና በመቆም በ UNHCR (United Nations High Commissioner for Refugees) የበጎ ፈቃድ አምባሳደር እንዲሁም ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ከ20 ዓመታት በላይ በማገልገል በሰሩት ሰፊ የሰብዓዊነት ስራ ይታወቃሉ።
/ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል /