
12/09/2025
ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ልጅን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ ያስጠይቃል
ሁሉም ት/ቤቶች ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ማስተማር ይጀምራሉ::
በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ መግለጹ ይታወቃል።
እነዚህን ልጆች ወደ ትምህርት ቤት የማስገባት ሀገራዊ ንቅናቄን በመቀላቀል የዜግነት ግዴታን በመወጣት ሁሉንም ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክቷል።
በሚኒስቴሩ የትምህርት ፕሮግራሞችና ሥርዓት ማሻሻል ዴስክ ኃላፊ ዳዊት አዘነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ክፍል ከተመዘገቡት ውስጥ ለ60 በመቶው የትምህርት ቤት ምገባ ተደራሽ ይደረጋል።
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ነጻ እና ግዴት መሆን በትምህርት ሕጉ መደንገጉን አስታውቀው፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት አለመላክ በሕግ እንደሚያስጠይቅም አሳስበዋል።
በ2018 ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 31 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለማስተማር መታቀዱን እና ከእነዚህ መካከል 15 ሚሊዮኑ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሰላም ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች፣ በኢኮኖሚ እጥረት እና የልጆችን ጉልበት በመፈለግ ምክንያት በ2017 የትምህርት ዘመን ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደነበሩም አውስተዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታ ላይ እንዲገኙ የታቀደው 31 ነጥብ 9 ሚሊዮንም ባለፈው ዓመት ከትምህርት ገበታ ውጭ የነበሩትን እንደሚያጠቃልል አስታውቀዋል።
ዕቅዱን ለማሳካትም ሚኒስቴሩ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የተማሪዎች ተሳትፎ የንቅናቄ ሠነድ አዘጋጅቶ ከክልሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ትምህርት ቤቶች ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለትምህርት ክፍት ሆነው ማስተማር እንደሚጀምሩም አስታውቀዋል።