
23/09/2025
የእግር ህመም መንስኤዎችና መፍትሔወች
አብዛኛው የእግር ህመም በመገጣጠሚያዎች ፣ በአጥንቶች ፣ በጡንቻዎች ፣ በጅማቶች ወይም ሌሎች ህብረ ህዋሶች መዳከም እና ከመጠን በላይ መጠቀም ወይም በአደጋ ምክንያት ሊከሰት ይችላል። አንዳንድ የእግር ህመም ዓይነቶች በታችኛው አከርካሪ ላይ ካሉ ችግሮች ጋር ሊያያዙ ይችላሉ፡፡ የእግር ህመም በደም መርጋት ፣ ቫሪኮስ ቬን ወይም በቂ የደም ዝውውር ባለመኖሩ ምክንያት ሊከሰት ይችላል
የእግር ህመም ምክንያቶች
▸ የሪህ በሽታ
▸ የደም መርጋት ችግር
▸ የአከርካሪ ችግር
▸ የሳያቲካ ችግር
▸ የአጥንት ኢንፌክሽን
▸ ውልቃት
▸ ቫሪኮስ ቬን
▸ የኩላሊት በሽታ
▸ የነርቭ ችግር
▸ ኢንፌክሽኖች
▸ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ አደጋዎች
የእግር ህመም አይነቶች
▸ ሺን ስፕሊንት (Shin splints) ፡- ፊት እግርዎ ወይም ቁርጭምጭሚትዎ ላይ ህመም ከጀመረዎ ብዙ ጊዜ የሺን ስፕሊንት ምልክት ነው ። ይህ ህመም የሚፈጠረው በእንቅስቃሴ እግራችን ላይ ጫና ስንፈጥር ነው። ሰውነታችን ከለመደው ደረጃ በላይ እንቅስቃሴ ስናደርግ ስሜቱ ይፈጠራል
▸ የእግር እስትራፖ ፡- ከፍተኛ እንቅስቃሴ ወይም የውሃ ጥማት እግር ላይ የጡንቻ መሳሳብ ወይም እስትራፖ እንዲፈጠር ያደርጋል አንዳንድ ግዜ ከተለመዱ ነገሮች ወጣ ያሉ ነገሮችን ስናደርግ ለእንደዚህ አይነት ችግር እንድንጋለጥ ያደርገናል
▸ የቁርጭምጭሚት ህመም ፡- ሲንቀሳቀሱ ወይም ቁርጭምጭሚትን ሲጫኑ የህመም ስሜቱ የሚጨምር መቅላት ወይም እብጠት ካለው የቁርጭምጭሚት ህመም ሊኖርብዎ ይችላል
▸ ሳያቲካ (Sciatica) ፡- ጀርባዎ እና የእግርዎ ጀርባ ላይ የሚወረወር ህመም የሚሰማዎት ከሆነ ችግሩ ሲያቲክ ነርቭ ላይ ሊሆን ይችላል። ሲያቲክ ነርቭ ከታችኛው ጀርባ ላይ ጀምሮ በመቀመጫ በማለፍ ወደ እግር የሚሄድ ነርቭ ነው
▸ የአኪሊስ ቴንደን ጉዳት ፡- ከተረከዝ በላይ የሚፈጠር ህመም ብዙ ግዜ የአኪሊስ ቴንደን ጉዳት ምልክት ነው። ከፍ ያለ የሂል ጫማ ማዘውተር ይህንን ህመም ይፈጥራል ፡፡ እንዲሁም ልጆች ከእንቅልፋቸው በእግር ህመም እና ስትራፖ ምክንያት ሊነሱ ይችላሉ የልጅ አጥንት ሲያድግ የጡንቻ ቴንደኖች በመለጠጥ ከአጥንት ጋር ሲያያዙ ህመም ሊፈጠር ይችላል
▸ የታፋ ህመም ፡- የቀን ሰራተኞች እና ሌሎች ከፍተኛ ጭነት የሚሸከሙ ሰዎች በታፋ ህመም በመጠቃት ይታወቃሉ ። የዚህ ምክንያት ዳሌ ዙሪያ የሚገኝ ነርቭ ላይ ጫና በመፈጠሩ ነው
የመከላከያ መንገዶች
▸ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል
▸ የሰውነት ክብደትን መቀነስ
▸ ቀለል ያሉና ምቾት የሚሰጡ ጫማዎችን መጠቀም
▸ የኩላሊት ፣ የጉበት ፣ የልብና የደም ግፊት በሽታዎችን በወቅቱ መታከም ዋንኞቹ የእግራችንን ጤና መጠበቂያ መንገዶች ናቸው
ለእግር ህመም የሚሰጡት የህክምና ዓይነቶች ከቀላል የነርቭ ህክምና እስከ ቀዶ ህክምና ድረስ የሚዘልቁ ሲሆን በደም ዝውውር መዘጋት ሳቢያ ለተከሰተ የእግር ህመም የተዘጋውን የደም ዝውውር በመክፈት የታማሚውን ጤና ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል የህክምና ዘዴ አለ።