20/02/2022
ዓባይ ለኢትዮጵያ ብርሃን መስጠት ጀመረ
On Feb 20, 2022 331
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 375 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን የታላቁ ህዳሴ የግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሂደትን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
የዓባይ ወንዝ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የስነ ቃልና ይትባሀሉ የቁጭት፣ የእንጉርጉሮና የወቀሳ ዜማ ሆኖ ኖሯል።
ዓባይ ማደሪያ ቢስነቱ በሊቃውንትና ጠቢባን አርዕስት ሆኖ ለዘመናት ተወቅሷል።
የዐባይ ውኃ መጠጥ ሆኖ እንዲጠጣ፣ መና ሆኖ እንዲጎረስ፣ ሲሳይ ሆኖ እንዲቆረስ የእልፍ ኢትዮጵያውያን ምኞት ነበር።
በትችትና ምኞት፣ በተስፋና ወቀሳ የተወገረው የዓባይ ወንዝ ግንድ ይዞ ዟሪነቱ ሊገታ፣ የልጅ ባዕዳነቱ ሊያከትም፣ ማደሪያ ቢስነቱ ሊቆም…የተወጠነው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥንስስ ነበር።
በወርሀ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉባ ወረዳ የግንባታው የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በህዝብ የድጋፍ ማዕበል ታጅቦ፣ በጠላት ዐይን ተገርምሞ፣ ዳፋና ተግዳሮቶችን ተሻግሮ ከ11 ዓመት በኋላ … የተስፋ ፍሬው ተቀመሰ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት መረጃ መሰረት የዋናው ግድብ ከፍታ 145 ሜትር ሲሆን÷ ርዝመቱ ደግሞ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።
የዋናው ግድብ ውፍረት የግድቡ ግርጌ ላይ 130 ሜትር፤ የግድቡ ጫፍ ወይም የላይኛው ክፍል ደግሞ 11 ሜትር ነው።
1 ሺህ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቦታ ስፋት ያለው ግድቡ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የውሃ መጠን ይይዛል።
ከ375 እስከ 400 ሜጋ ዋት የሚያመየጩ 13 የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች አሉት።
ኢትዮጵያ ከግድቡ አመንጭታ ፍጆታዋን ካሟላች በኋላ 2 ሺህ ሜጋዋት ገደማውን ለጎረቤት አገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደምትችል ግምቶች ተቀምጠዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ተከታታይ የክረምት ዝናብ የመጀመሪያና ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት ተከናውኗል።
ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃ የሚተኛበት መሬት 246 ኪሎ ሜትር ይረዝማል።
ዛሬ 375 ሜጋዋት የሚያመነጨው አንደኛው ዩኒት በይፋ ስራ ጀምሯል። ሁለተኛው ዩኒት ደግሞ በዝግጅት ላይ ይገኛል።
የግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ ሲጠናቀቅም 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የኤክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ይሆናል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://m.facebook.com/109776264766956/