
30/05/2022
እስራኤል ከአልቡርሃን ጋር ግንኙነት እንዳታደርግ አሜሪካ አሳሳበች
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት እስራኤል ሲቪል መንግስት ገልብጦ በወታደሮች የሚመራ መንግስት ከመሠረተው አካል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ከማደስ እንድትቆጠብ አሳሳበ፡፡
“እስራኤል ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን በመቀላቀል በይፋ ወታደራዊው አመራሮች ላይ ጫና እንድትፈጥር እንዲሁም ተዓማኒነት ላለው የሲቪሊያን መንግስት ሥልጣኑን እንዲያስርከብ እየተደረጉ ያሉ ርብርቦችን እንድትደግፍ እናበረታታለን” ብሏል መግለጫው፡፡
እንደ አሜሪካ መግለጫ በአልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊው ክንፍ በሲቪል መንግስት ላይ ያደረገው መፈንቅለ-መንግስት አሁን ላይ ከአገሪቱ ጋር ግንኙነት ማድረግን አስተማማኝ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ሱዳን ለጊዜው ወዳጅነቷን ለማሻሻል ከምታደርገው ጥረት ይልቅ ሱዳን ወደ ሰላም እንድትመለስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንድትቀላቀል ግብዣ አድርጓል፡፡
በፕሬዝዳንት ትራምፕ አግባቢነት በአረብ አገራትና በእስራኤል አገራት መካከል የተደረሰው “የአብርሃም ስምምነት” በዩ.ኤ.ኢ፣ ባህሬይን፣ ሞሮኮ እና ሱዳን ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሚሰረቱ ያደረገ ሲሆን ከሱዳን በስተቀር የሌሎቹ ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡
እስራኤል ከሱዳን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በፍጥነት እንዲከናወን ፍላጎቱ የነበራት ቢሆንም የሱዳን የውስጥ አለመረጋጋት፣ መፈንቅለ መንግስት እና ወታደራዊ አመራሮቹ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ እያስተናገዱ ያሉት ተቃውሞ ግንኙነቱን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ አልቡርሃን ልዑካኖቹን ወደ እስራኤል በተደጋጋሚ በመላክ ጉዳዩ በቶሎ እንዲያልቅ በዛውም ተቃዋሚ ሰልፈኞችን መበተን የሚያስችል ድጋፍ ከእስራኤል እንዲሰጠው ሲጠይቅ ነበር፡፡
አልቡርሃን “ከእስራኤል ጋር የሚኖረውን ፖለቲካዊ ግንኙነቱን የሚመረጠው የሲቪል መንግስት የሚያከናውነው በመሆኑ እኛ የጸጥታ ትብብር ብቻ ነው ያደረግነው” ማለቱ ተቃዋሚዎችን በብልሃት ለማስወገድ ከእስራኤል የስለላ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማግኘት ነው ሲሉ ለውጥ ፈላጊዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፡፡
አልቡርሃን በግብጽ አማላጅነት የእስራኤልንና የአሜሪካን ልብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም ከአሜሪካ ድጋፍ ውጭ እስራኤል ከሱዳን ጋር ግንኙነት መመስረት የማትችል በመሆኑ ለጊዜው የአልቡርሃን ህልም መጨናገፉ አይቀሬ ይመስላል፡፡
ተሰሚነት ያላቸው የሱዳን ተቃዋሚዎች እስራኤል ከአሁኑ ወታደራዊውን መንግስት በመቃወም አቋሟን ግልጽ ካላደረገች ወደ ፊት ከሚኖረው የሲቪል መንግስት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል እያሉ ነው፡፡
እስራኤል በይፋ ወታደራዊውን መንግስት መቃወም ባትፈልግ እንኳን ቀስ ቀስ እያለች ማፍግፈጓ አይቀሬ በመሆኑ አልቡርሃን ከአስራኤል የፈረጠመ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ተቋድሼ ተቃዋሚዎቼን አጠፋለሁ የሚለው ምኞቱ መና ይሆናል የሚል እምነት በሱዳን ልሂቃን በስፋት የታመነበት ጉዳይ ነው፡፡
Abay Tube
የዩቲዩብ ቻናል
•YouTube: - https://www.youtube.com/channel/UCvOuOX2nVqsK_gX-J0fcvsw
•Facebook: - https://www.facebook.com/AbayOnYoutube/
•Instagram: - https://www.instagram.com/abayentertainment
•Telegram: - https://t.me/AbayonYouTube
ስብስክራይብ ማድረጉዏን እንዳይረሱ ስለጉበኙን እናመሰግናለን።