
28/10/2021
ከአውሎ ሚዲያ የተሰጠ መግለጫ
የተከበራችሁ የአውሎ ሚዲያ ተከታታዮች:- ድርጅታችን አውሎ ሚዲያ ሴንተር ባለፉት ሶስት አመታት በበይነ መረብ የሚዲያ ዘርፍ ላይ በመሰማራት በርካታ የሚዲያ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብና ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ገንቢ ሚና በመያዝ በተለይም የተራራቁ ፅንፍ ሃሳቦችን በማቀራረብና ብሎም እኩል ድምፅ በመስጠት በዘርፉ የሚፈጠሩ ወገንተኛነትና አግላይንት በመስበር በርካታ ስራዎችን ለአድማጭ ተመልካች ሲያደርስ ቆይቷል፡፡
ድርጅታችን እነዚህን ተግባራት ሲያከናውን ግልፅና ህጋዊ አሰራርን በመተግበር ነው፡፡ ለዚህም ግልፅ የሆነ የኤዲቶሪያል አሰራርን በመተግበር፤ ግልፅ የሆነ የፋይናስ አስራርን በመከትል ፤ ከመንግስት የንግድ ፈቃድ ፡የፕሮዳክሽን ፈቃድ እና የበይነ መረብ ፈቃድ በመውሰድ ነው፡፡
ድርጅታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያቀርባቸውን ስራዎች ጥራትና ሙያዊ ደረጃ እያሻሻለ በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም በርካታ ተመልካቾችን በማፍራት ተወዳጅነቱን ከፍ አድሮጎ ነበር፡፡ በተለይም የህዝቦችን አብሮ መኖር ፤እርቅና ስምምነትን ፤ ሰላማዊ ውይይትና ድርድርን ፤ የፍትህ መጓደልን ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን በተመለከተ እንዲሁም ሃገራችን ብሄራዊ ጥቅምና እድገት የሚያስረዱ የሚተነትኑ ዝግጅቶቻችን የብዙዎችን ቀለብ የሳቡ ነበሩ፡፡
ነገር ግን ባለፈው ሰኔ 23/2013 ዓ.ም መንግስት የፌዴራል ፖሊሲን በመላክ በርካታ የድርጅቱን ንብረቶች ከመውሰዱም በላይ የስራ ቦታውን ሙሉ በሙሉ በማሸግ ፤ የድርጅቱን ሰራተኞች ኢ ፍትሃዊ በመሆነ መንገድ አፋር ክልል አዋሽ ሰባት የፈዴራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ በማሰርና በማፈን ከፍተኛ ግፍ ፈፅሞባቸዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተቋማት ባደረጉት ጥረት ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ፍርድ ቤቱም እንዲለቀቁ በመወሰኑ ከበርካታ እንግልትና ስቃይ በኋላ ተለቀዋል፡፡ የፍትሕ ተቋማቱ የድርጅቱን ሰራተኞች እንዲለቀቁን ብሎም የድርጅቱም ሆነ የሰራተኞቹ የግል ንብረት እንዲመለስና ፖሊስ ያሸገው የድርጅቱ ቢሮ እንዲከፈት ቢወስኑም እስካሁን ድርስ ከፌዴራል ፖሊስ ይህ ነው የሚባል ህጋዊ መልስና ተግባር ሊገኝ አልቻለም፡፡
አውሎ ሚዲያ ያሉትን ሰራተኞች ህጋዊ ቅጥራቸውን በማስቀጠል እስከ ዛሬ ድረስ ከመንግስት ተቋማት መፍትሄ እየጠየቀ የቆየ ቢሆንም ሁሉም የመንግስት ተቋማት ማለትም የፌዴራል ፖሊስ ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እና የሚመለከታቸው ተቋማትና ሃላፊዎች እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህ ነው የሚባል ህጋው መፍትሄም ሆነ እርምጃ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡
ስለሆነም ድርጅቱ በመንግስት በተፈጠረ ችግር ምክንያት ሰራተኞችን ሙሉ በሙሉ አሰናበቷል ፡፡ የተከበራችሁ የድርጅታችን ሰራተኞች በነበሩን እጅግ ፈተና የበዛባቸው የስራ ጊዚያት ሙያችሁ የሚፈቅደውን መብትና ግዴታዎች በማክበር በታማኝነት ድርጂቱን በማገልገላችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባል፡፡
የተከበረውን የሚዲያ ዘርፍ ተጠቅማችሁ ለህዝብ ስትሉ ሃቅ በመስራታጭሁና እውነትን በመነፍነፍ ለተበደሉ ዜጎች ድምፅ በመሆናቸሁ በመንግስት ለፈጻመባችሁ በደል ድርጅቱ ከፈተኛ ሃዘን ተስምቶታል፡፡ ውድ ሰራተኞቻችን በተአማኒነት ሀገርና ወገን ለማግልግል የነበራችሁን ቁርጠኝነት እያደነቅን ለነበረን እጅግ ወርቃማ የስራ ጊዚያት ድርጅቱ እያመሰገነ በመንግስት በደረሰባችሁ በደልና ኢ ፍትሃዊ ተግባራት ሁሉ ፍትህ ባለመግኘቱና ወደ ምትወዱት ሙያና ተቋም ባለመመለሳችሁ እናዝናለን፡፡ በቀጣይም በርትታችሁ የምተሰሩበት ተቋምና ስራ እንዲገጥማችሁ እየተመኘን ለነበረን ጊዜ ሁሉ እናመሰግናለን፡፡
ክቡራንና ክቡራት የአውሎ ሚዲያ ተከታታዮችና ቤተሰቦች መንግስት ሆን ብሎና አስቦ ባደረሰብን ኢ ፍትሃዊ በደልና ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ስራችን መመለስ ባለመቻላችን ይቅርታ እየጠየቅን ለነበረን አብሮት እጅግ እናመሰግናለን፡፡
አውሎ ሚዲያ ግልፅ በሆነ መንገድ በመንግስት በተፈፀመበት በደል ለመዝጋት በመገደዱ በትጋት መረጃ በማሰራጨት ሲያገለግሏችሁ የነበሩ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ማሰናበቱን እንድትረዱልን እናሳሳባለን፡፡
ድርጅታችን አውሎ ሚዲያ ሴንተር አሁንም ኢ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመንግስት የተወሰዱብን በርካታ ንብረቶች እንዲመለሱልን ፤ የድርጀታችን ቢሮም እንዲከፈትልን እየጠየቅን ፤ መንግሰት የሚዲያ ምህዳሩን እጅግ ከሚያጠቡና ከሚያቀጨጩ ተግባራት በመቆጠብ በዘርፉ ያሳየውን መጠነኛ ነፃነት ከመጥፋት እንዲታደገው ጥሪ እናቀርባለን፡፡
አውሎ ሚዲያ
ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም