01/05/2025
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 44ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት እና ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረሙ ሁለት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግስት የተገኘው የ11,500,000 ዩሮ ለአካባቢያዊና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን የ16 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው 38,100,000 ኤስ.ዲ.አር ለመማር ማስተማር ማጎልበቻ የትምህርት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት ሆኖ 6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱም ብድሮቹ ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብባቸው እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን መቋቋሚያ ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ትኩረቱን በመሠረተ ልማት፣ በተፈጥሮ ሀብት እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ላይ በማድረግ ለግል አልሚዎችና ለመንግሥት አካላት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመ ነው፡፡ ሀገራችን በአባልነት መቀላቀሏ ለግሉ ዘርፍ ተጨማሪ የፋይናንስ ሀብት በማቅረብና የግል ዘርፉን የማይተካ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት ሚና በማሳደግ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠንና ድህነትን ለመቀነስ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ሌላው ምክር ቤቱ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት የዕቃዎች ቀረጥ ምጣኔ ቅነሳን ለማስፈፀም በቀረበ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል። ስምምነቱ በአባል ሀገራት መካከል ንግድ እንዲስፋፋ፣ የገበያ ትስስሩ እንዲጠናከር፣ የእሴት ሠንሰለቱ እንዲጎለብት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማበረታታት የሚያስችል ነው፡፡ በአባል ሀገሮች መካከል የሚደረጉ ግብይቶች በታሪፍ ምክንያት ሳይደናቀፉ የእቃዎች ፍሰት የተሳለጠ እንዲሆን ከአባል አገራት በሚመጡ እቃዎች ላይ የጉምሩክ ታሪፍ ምጣኔ ለይቶ መወሰን አስፈላጊ መሆኑን በመወያዬት ምክር ቤቱ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለሚሰጡ አገልግሎቶች እና በኢ.ፌዲ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ለሚሰጡ አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ሁለት ረቂቅ ደንቦች ላይ ነው፡፡ ተቋማቱ አገልግሎት ለመስጠት የሚያወጡትን ወጪ በመሸፈን፣ ገቢያቸውን አሳድገው ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታ ማሳደግ የሚያስችል የደንበኞችን አቅም ባገናዘበ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ መወሰን አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቦቹ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ