13/12/2025
14 የሥራ አመራር አባላት ከሃላፊነታቸው ተሰናበቱ
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ECWC) በውስጡ ያለውን "የአፈጻጸም፣ የተጠያቂነት እና የመልካም አስተዳደር ክፍተት" ለማረም በሚል የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ፤ 14 የሥራ አመራር አባላትን ከሃላፊነታቸው ማሰናበቱን አስታወቀ።
በቅርቡ የተሾሙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮቤል ፀጋዬ በታህሳስ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ለሰራተኞች ባስተላለፉት የውስጥ ማስታወሻ እንዳመለከቱት፤ የኮርፖሬሽኑ የቦርድ አመራር ባደረገው ጥልቅ ግምገማ በተቋሙ ውስጥ ከፍተኛ የአፈጻጸም ክፍተቶች ተገኝተዋል።
በግምገማው የተለዩት ዋና ዋና ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፦
• የፕሮጀክት አፈጻጸም በቋሚነት ከሚጠበቀው በታች መሆን፣
• የኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ አቅም ያዳከሙ የስትራቴጂክ ውሳኔዎች መኖር፣
• ቁልፍ የአሰራር ስርዓቶች፣ የቁጥጥር እና የአስተዳደር ልምዶች እንደተፈለገው አለመስራት፣
• የተጠያቂነት እና የአመራር ቅንጅት ማነስ።
እነዚህን ችግሮች ተከትሎ የቦርድ አመራሩ የተቋሙን እና የሀገርን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል፤ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ተግባራዊ በሚሆን ውሳኔ የሚከተሉት 14 የስራ አመራር አባላት ከስራ እንዲሰናበቱ ወስኗል።
ከሃላፊነት የተነሱት አመራሮች ዝርዝር፡
1. አቶ አሰፋ ቀሴቶ
2. አቶ በምነት ጋሻው
3. ዶ/ር ቤዛዊት ግርማ
4. አቶ ኢሳያስ አንዳርጌ
5. አቶ ፍፁም ታምሩ
6. አቶ ሳሙኤል አማረ
7. አቶ ሸዋንግዛው ተስፋዬ
8. አቶ ሱራፌል አባይነህ
9. አቶ ታደለ ፉሌ
10. አቶ ዋቅጅራ ይልማ
11. አቶ ወገን ሰለሞን
12. አቶ ዮሃንስ አየለ
13. አቶ ዘሪሁን መኩሪያ
14. ወ/ሮ ዘይነባ ኡመር
ይህ እርምጃ የተወሰደው የአመራር ድክመቶችን ለማረም፣ ግልፅነትን ለማስፈን እና ኮርፖሬሽኑን ወደ ተሻለ የፕሮጀክት አፈጻጸም ለመመለስ እንደሆነ ዋና ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።
በተጓደሉት ቦታዎች ላይ ጊዜያዊ አመራሮች እንደሚመደቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ሁሉም ሰራተኞች ይህ የሽግግር ወቅት እስኪያልፍ ድረስ ሃላፊነታቸውን በዲሲፕሊን እንዲወጡ አቶ ሮቤል አሳስበዋል።