03/03/2026
የቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ በሕይወት መኖራቸው ተረጋገጠ
የቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ ደህንነታቸው የተጠበቀና በሕይወት እንደሚገኙ የቅርብ አማካሪያቸው ለአናዶሉ የዜና ወኪል ገለጹ።
አሜሪካና እስራኤል በጋራ በመሆን የኢራንን ከፍተኛ አመራሮችና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ባደረገ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ አህመዲነጃድ ተገድለዋል የሚሉ ዘገባዎች ተሰራጭተው ነበር። ሆኖም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት አማካሪያቸው “ከእሳቸው ጋር ተገናኝቻለሁ ሁሉም ነገር ሰላም ነው” ሲሉ ወሬውን አስተባብለዋል።
እንደ አማካሪው ገለጻ ትናንት በተሰነዘረው ጥቃት ከአህመዲነጃድ የደህንነት ጥበቃ ጋር ግንኙነት ያለው ሕንፃ ተመትቷል በጥቃቱም
የኢራን አብዮታዊ ዘበኛ (IRGC) አባል የሆኑ ሦስት የግል ጠባቂዎቻቸው ተገድለዋል የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ቤት ጥቃቱ ከፈጸመበት ሕንፃ 100 ሜትር ያህል ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ቤቱ ኢላማ አልተደረገም እንዲሁም ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም።
ማህሙድ አህመዲነጃድ ከ2005 እስከ 2013 እ.ኤ.አ. ድረስ በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን ይህ ማረጋገጫ የተሰጠው በእስራኤልና አሜሪካ የአየር ድብደባ ተገድለዋል የሚለው መረጃ በስፋት ከተሰማ በኋላ ነው።