15/09/2025
የስልጠና ሉዓላዊነት አሁኑኑ!
በጋዜጠኛ ሀይለ እግዚአብሔር አድሀኖም
ለከራረመው የአትሌክሳችን ውጤት መራቅ ምክንያት ይሆናሉ ብለን ስለ የቡድን ስራ መጥፋት: ታክቲክ፣ የአየር ሁኔታ፣ የትውልዶች መለያየት እና ሌሎችም ማውራት እንችላለን:: ተገቢ እና ውሃ የሚያነሱ ሀሳቦችም ናቸው:: ነገር ግን ትኩረት የሚሻው ሌላውና ዋናው ችግር "የስልጠና ሉዓላዊነታችንን" ማጣታችን ነው ብዬ አምናለሁ።
እንዴት?
አሁን ላይ የስልጠና ስልቶቻችን፣ ልማዶቻችን እና አመጋገባችን፣ ሁሉንም መርሐግብር በሚያዘጋጁልን ጥቂት አውሮፓውያን እጅ ስር ጠቅልሎ ከገባ ሰነባበተ::
የአብዛኛዎቹ የሀገር ውስጥ አሰልጣኞቻችን ሚናም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ተራ ሰዓት ያዥነት እና ከሌላ ቦታ ተዘጋጅቶ የሚመጣውን የስልጠና እቅድ ሳይሸራርፉ ተግባራዊ ወደ ማድረግ እያሽቆለቆለ ይገኛል።
ይህንን በማድረጋችንም የስልጠና ሉዓላዊነታችንን ብቻ ሳይሆን የነበረንን የውጤት የበላይነታችንንም አጥተናል።
የራሳችን አሰልጣኞች ዘመናዊ ሳይንሱን: ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባህርይ እንዲስማማ አድርገው ያሰለጥኑ በነበረበት ወቅት:
እኛ የበላይነት ነበረን።
ማንነት ነበረን።
ውጤትም አግኝተንበት ነበር።
አዲሱ እውነታ
አሁን አሁን፣ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውጤታማነት በሚታወቁባቸው የውድድር አይነቶች: ያልተለመዱ ሀገራት ሯጮች ውጤት ሲያስመዘግቡ እየተመለከትን እንገኛለን::
በተለይም በተመሳሳይ የአትሌት ማኔጅመንት ስር በሚተዳደሩ በየትኛውም የአለም ክፍል በሚገኙ አትሌቶች መካከል ያለው የአቋም እና የውጤት ልዩነት በእጅጉ እየጠበበ መምጣቱ የአደባባይ ሀቅ ከሆነ ከራረመ:: ለዚህ አዲስ እውነታ ከዋነኛ ምክንያቶቹ አንዱ ደግም የስልጠና ሂደቶቹ የሚቀዱት በአብዛኛው ከተመሳሳይ ቋት መሆኑ ነው::
ነገር ግን እንዲህ እንጠይቅ እስኪ: ለመሆኑ:
የሥልጠና ሥርዓቶቻችንን የሚያዘጋጁልን አካላት: በተለያዩ ሀገራት አትሌቶች መካከል ምንም ዓይነት አድልዎ ላለማድረጋቸው ማረጋገጫችን ምንድን ነው?
የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዝግጅት እና የውድድር ታክቲክ ለተፎካካሪወቻቸው ቀድሞ አለመድረሱን ማን ማስተማመኛ ይሰጠናል?
አትሌቶቻችንን ከዶፒንግ አደጋ የምንጠብቅበት የደህንነት ሁኔታስ ልብ የሚያሳርፍ ነው? ወዘተ...
ጥቂት የመፍትሄ ነጥቦች:
ፌዴሬሽኑ የቴክኒካል ዲፓርትመንቱን በራዕይ እና በተጠያቂነት እንዲመራ እንደገና ማዋቀር እና ማብቃት።
ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምሁራን እና የዓለም አትሌቲክስ ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር: የሚገኙ አወንታዊ አቅሞችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም።
በሁሉም የስልጠና እርከኖች የሚተገበር: ኢትዮጵያ መር: ቀጣይነት ያለው የአሰልጣኝነት የአቅም ግንባታ እና ምዘና መርሃ ግብሮችን በየደረጃው ተግባራዊ ማድረግ።
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ አሰልጣኝነትን ለማጥናት፣ ለማሳደግ እና አዳዲስ ፈጠራ መር የአሰለጣጠን መንገዶችን ለመማር የሚያስችል "የልህቀት ማእከል" እስከመመስረት ድረስ በትልቁ ማሰብ::
እነዚህን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ ጠቃሚ ምክረሀሳቦችን ወደ ተግባር ከለወጥን: በእርግጥም: ማንነታችንን እናስከብራለን፣ አሸናፊነታችንን እናስጠብቃለን እንዲሁም ቀጣዩን ድል አድራጊ ትውልድ በሚገባ ለማዘጋጀት እንችላለን።
አዎ: የስልጠና ሉዓላዊነት አሁኑኑ !
ባላገሩ ስፖርት