21/11/2025
የተመረዘ ምግብ በልተዉ ከታመሙ 8 የአንድ ቤተሰብ አባላት ዉስጥ የ7ቱ ህይወት አለፈ
ምግቡ በማንና እንዴት ተመረዘ?
ሆሳዕና ህዳር 12 ቀን 2018 (ማ.ኢ.ፖ.ኮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በአብሮነት እራት ተመግበዉ በጠና ከታመሙ ስምንት የአንድ ቤተሰብ አባላት ዉስጥ አባወራዉ ከስድስት ልጆቹ ጋር ሰባት የአንድ ቤተሰብ አባላት ህይወታቸዉ ማለፉን ፖሊስ ገልጿል።
የክልሉ ፖሊስ የወንጀል መረጃ ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ተወካይ ምክትል ኮማንደር ያለዉ ተመስገን እንደገለፁት በወረዳዉ መሰረተ ወገራም ቀበሌ ዳሾ ቆቶ ተብሎ በሚጠራዉ መንደር ህዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 1:00 ሰዓት ስምንቱ የቤተሰብ አባላት አብረዉ እራት ከተመገቡ በኋላ በድንገት መታመማቸዉ ተናግረዋል።
በአብሮነት እራት እንደተመገቡ ብዙም ሳይቆዩ ከፍተኛ ለሆነ ህመም መዳረጋቸዉን መረጃ የደረሳቸዉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች የተጎጂዎችን ህይወት ለማትረፍ ተረባርበዉ ወደ ሆስፒታል ማድረሳቸዉ ነዉ የተነገረዉ።
ቢሆንም ከተጎዱ የቤተሰቡ አባላት የ5 ዓመቱ መንግስቱ ኃይሌ ፣የ7 ዓመቱ መክብነ ኃይሌ እና የ17 ዓመቱ ተክሉ ኃይሌ የተባሉት ሶስቱ ወንድማማቾች በዕለቱ ሆስፒታል እንደደረሱ ህይወታቸዉ ማለፉን ነዉ የተገለፀዉ።
የተቀሩ ተጎጂዎችን ህይወት በህክምና ለማትረፍ ሀኪሞች ያልተቋረጠ ጥረት ቢያደርጉም የ14 ዓመቷ መቅደስ ኃይሌ እና የ15 ዓመቱ ገብሬ ኃይሌ የሁለቱ እህትና ወንድም ህይወት ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 11:00 ሰዓት ሲያልፍ የሟቾች ቁጥር ወደ አምስት አሻቀበ።
ከተቀሩት ተጎጂዎች ደግሞ የ1ዓመት ከ7 ወሩ ህፃን ሲሳይ ኃይሌ ህዳር 9 ቀን 2018 ዓ.ም ጥዋት 2:00 ሰዓት ላይ ህይወቱ ሲያልፍ የስድስቱ ሟች ልጆች አባት የሆነዉ አቶ ኃይሌ አበራ ህዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ለሊት በሰመመን ዉስጥ ሆኖ ከእንቅልፉ ሳይነቃ ህልፈቱ እዉን ሆኖ ልብ ሰባሪና አሳዛኝ የሆነ ዜና ተደመጠ።
የባለቤቷንና የስድስት ልጆችዋን ህልፈት ለማወቅ ያልታደለችዉ ወይዘሮ ዳመነች ደንበል በሚኒሊክ ሆስፒታል በከፍተኛ የጥንቃቄ ክፍል ዉስጥ ሆና በህክምና እየተረዳች በህወት መኖሯን ነዉ ፖሊስ የተገለፀዉ።
ተጎጂዋ ቤተሰቡን በጅምላ ወደ ሞት ያወረደዉን ጉዳይ ልትተርክ በህይወት ትተርፍ ይሆን?ወይስ እሷም የባለቤቷና የልጆችዋ እጣ ገጥሟት ከቤተሰቡ መሀል አንድም ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ በጅምላ እቺን አለም የመሰናበታቸዉ አሳዛኝ ዜና ይደመጣል? የሚለዉን ለመገመት ይከብዳል።
ፖሊስ ተጎጂዎች የተመገቡት ምግብ የተመረዘዉ በማንና እንዴት?የሚለዉን እዉነታ ለማረጋገጥና የተፈፀመዉን ድርጊት አጣርቶ እዉነታዉ ለማረጋገጥ ከምስራቅ ጉራጌ ዞን እና ከመስቃን ወረዳ የተወጣጣ የምርመራ አጣሪ ግብረ ኃይል አዋቅሮ ምርመራ የማጣራቱን ስራ መጀመሩን የተናገሩት ኮማንደር ያለዉ ተመስገን የምርመራ ግብረ ኃይሉ በድርጊቱ የሌሎች እጅ ሊኖር ይችላል በሚል ጥርጣሬ አስር ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዉሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልፀዋል።
ተጎጂዎች በዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ህክምና ተከታትለዋል ያለዉ ፖሊስ የሟቾች የአስክሬን ምርመራ ዉጤት እየተጠበቀ መሆኑንና ስለጉዳዩ የተሻለ ፍንጭ ሊሰጥ እንደሚችል መረጃ ሊገኝ እንደሚችል ይገመታል። የክልሉ ፖሊስ ሚድያ ክፍል ይህ ዜና በሚድያ ይፋ እስካደረገበት ሰዓት ድረስ ከስምንቱ ተጎጂዎች ዉስጥ አንዷ የሆነችዉ የቤቱ እማወራ በአዲስ አበባ ምንሊክ ሆስፒታል በህክምና እየተረዳች መሆኑን አረጋግጧል።መረጃው የክልሉ ፓሊስ ነው ። ታጁ ነጋሽ።