26/03/2025
(ብራና ሚዲያ)
ዩትዩብ ወይም ቲክቶክ የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ገንዘብ የሚያገኙ ግለሰቦች እና ተቋማት ታክስ እንዲከፍሉ ሊደረግ ነው።
በክፍያ የሚቀርቡ ወይም በሚያቀርቡት አገልግሎት ገንዘብ ከሚያገኙ የድረገጽ እና የመተግበሪያ ውጤቶች ላይ መንግሥት ታክስ ሊሰበስብ መዘጋጀቱን አሰራሩን ለመተግበር ከወጣው የመንግሥት ሰነድ መመልከቱን ዋዜማ ሬድዮ ዘግቧል።
በድረገጽ የሚቀርቡ የሚዲያ አገልግሎቶች ፖድካስት፣ ፊልም ፣ ሙዚቃን ጨምሮ በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም ቫት ይጣልባቸዋል።
በደምበኝነት ምዝገባ ላይ የተመሰረተ የሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ የሚያስገድደው አሰራር በኤሌክትሮኒክስ ዘንዴ በሚቀርብ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ እሴት ታክስ እንዲካተት አድርጓል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የፀደቀው የተጨማሪ እሴት ታክስ ለማስፈጸም የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተጨማሪ እሴት ታክስ የተሰኘው ደምብ በ13 ክፍሎች እና በ66 አንቀፆች ተከፋፍሏል።
የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እንዲታወጅ ካስፈለገበት ምክንያት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ አዳዲስ እሳቤዎችን በሀገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ በማካከት ታክሱ ለኢኮኖሚው እድገት እገዛ እንዲያደርግ ማስቻል የሚለው ይገኝበታል።
በዚህ መሰረት ከዚህ ቀደም ተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ ያልተካተቱ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚቀርቡና የደምበኝነት ምዝገባ በመጠቀም የሚተላለፉ ሚዲያዎች ፣ መፅሄቶች፣ ጋዜጦች ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ሙዚቃዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ ተጥሎባቸዋል።
አሁን አዋጁን ለማስፈፀም የወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደምብ በየነመረብ በመጠቀም የሚተላለፉ ፖድካስቶች፣ ብሎጎች፣ ጆርናሎች ለመንግሥት ታክስ መክፈል እንዳለባቸው ያስገድዳል።
የማህበራዊ ትስስር አገልግሎት / ዌብሳይት እና መተግበሪያዎችን ማቅረብ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚታሰብባቸው አገልግሎቶች መሆናቸው ተመላክቷል።
በኤሌክትሪክስ ዘዴ ከሚቀርቡና ታክስ ከሚከፈልባቸው አቅርቦቶች ተከታከቱት ሌሎች አገልግሎቶች ውስጥ በበየነ መረብ የተመሰረተ የጨረታ አገልግሎት መስጫ አቅርቦት፣ የማንኛውም ዲጅታል ይዘት ያለው መፅሀፍ ወይም ህትመትን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክ መፅሀፍ አቅርቦት የሚሉት ይገኙበታል።
በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚጫኑ ዲጅታል ይዘት ያላቸው መተግበሪያዎች እና ፊልሞች በታክሱ ተካተዋል።
- የሙዚቃ አቅርቦት
- የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት
- የስልክ ጥሪ ድምጽ
- ለቀጥታ ዝግጅቶች፣ ትያትሮች እና ምግብ ቤቶች የሚውሉ ትኬቶችን በኢንተርኔት በኩል መሸጥ በአዋጁ መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ አገልግሎት የሚከደልባቸው ናቸው።
ደምቡ በኢትዮጵያ ግዛት በዲጅታል መንገድ የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት በተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ ተካቷል።
የመንገደኞችን የትራንስፖርት አገልግሎት በመመቻቸት በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መንገደኞችን ከትራንስፖርት አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኙ ማንኛውም ሰው ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ መሆኑንም በደምቡ ላይ ተብራርቷል።
የፕላትፎርም / በዲጅታል የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ ማናቸውም ክፍያዎችን እና ኮሚሽኖችን ጨምሮ ሌሎች ተሳፋሪዎች ከሚከፍሏቸው ጠቅላላ ክፍያዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ መሰብሰብ አለበት ሲል ደምቡ ያዛል።
የፕላትፎርም አቅራቢው በየዕለቱ መጨረሻ ለመንገደኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መስጠት እንዳለበት ደምቡ ያብራራል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የዋዜማ ራድዮ ነው።