11/06/2026
ከሚስቴ ጋር እንዳልታረቅ ምክንያት ሆናለች በማለት የገዛ ሚስቱን እህት የገደለዉ ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ
በኢሊባቡር ዞን ነዲ ናኖ ወረዳ ኮምበልቻ ከተማ ነዋሪ የሆነው ደበሌ በቀለ የ31 አመት ወጣት ሲሆን በ2012 ዓመት ትዳር መስርቷል።
የጥንዶቹ ጥምረት ሰላማዊና በአንዲት ሴት ልጅ የተባረከ እንደነበር በዞኑ ፖሊስ ዋና መምርያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አበራ አሠፋ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን ከ2018 ዓመት ወዲህ አለመግባባቶችና ግጭቶች ነበሩ። በዋነኝነት የግጭታቸው መንስኤ እቤት ውስጥ የነበረ ፍቅር ቀንሷል የሚል የሚስት ጥያቄ ሲሆን ይሕንን ለማስተካከል በባል በኩል የተወሠደ ማስተካከያ የለም በሚል ነዉ፡፡
አለመግባቱ በሂደት ከመፈታት ይልቅ እየተባባሠ በመሄዱ በትንሣኤ በዓል ሰሞን ሚስት ቤቷን ጥላ ሕፃን ልጇን ይዛ ወደ ቤተሠቦቿ ትሄዳለች።
ትመጣለች ብሎ የሚጠብቀው ባል ሽምግልና ቢልክም በሚስት ፈቃደኛ አለመሆን ነገሮች በእንጥልጥል ላይ እንዳሉ 21 ቀናት ተቆጠሩ።በነዚሕ ቀናት ለባል ተባራሪ ወሬዎች ይደርሱት ጀመር።
ይሕውም የባለቤቱ ታናሽ እሕት፣ እህቷ ወደ ትዳሯ እንዳትመለስ ግፊት ታደርጋለች የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ ነበር።በእህቷ ባል የተወነጀለችዉ የ18 ዓመት ወጣት በዘንድሮ አመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ የሆነችው ፌኔት አሠፋ ነች።
በተደጋጋሚ ፌኔትና የእህት ባል ተገናኝተው ቢያወሩም አንቺ ነሽ ወደ ትዳሯና ቤቷ እንዳትመለስ የምትመክሪያት የሚለው ያልተጨበጠ ጥርጣሬ ወደ ዛቻ ሲቀየር ፌኔት ጉዳዩን በጥንቃቄ መመልከት ጀመረች።
ይሕ ዛቻና ማስፈራርያ እየተጠናከረ መጥቶ ሚያዝያ 21 ቀን 2018ዓም ደረሠ የሚሉት ምክትል ኢንስፔክተር አበራ፣ በዚያን እለት ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ተኩል ላይ ፌኔት አሠፋ ከጓደኞችዋ ጋር ወደ ቤተ መፅሐፍት ቤት ስትጓዝ ....
በነዲ ናኖ ወረዳ በኮቦልቻ ከተማ ጤና ጣቢያ አካባቢ ጠብቆ በጀለብያ ሸሽጐ የያዘውን ገጀራ ስለታ ብረት በመያዝ አብሮዋት ካሉ ጓደኞቿ ነጥሎ በመጥራት ሠላማዊ ንግግር ካናገራት በኃላ ድንገት የደበቀውን ስለታም ገጀራ በማውጣት በአደባባይ፣ በጠራራ ፀሐይ ፣ ማጅራቷ ላይ በመምታት ይጥላታል።
ፌኔት በደረሠባት ምት ወድቃ ባለችበት ተከሣሽ በተደጋጋሚ በመምታት ባደረሠባት ጉዳት፣ ህይወቷ አልፏል፡፡ድርጊቱን የፈፀመው ተከሳሽ ወዲያው ሮጦ እጁን ለፖሊስ ይሰጣል።
ፖሊስም የወደቀችውን ታዳጊ ወጣት አስክሬን በማስነሣት ወደ መቱ ካርል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመላክ የምርመራ መዝገቡን ማደራጀት ይጀምራል።
በወቅቱም ቤቷን ጥላ ወላጆቿ ጋር የነበረችው የሟች ታላቅ እህት ለፖሊስ በሰጠችዉ የማስረጃ ቃል በሑለቱ ግጭት ሟች እህቷ ምንም የምታቀው ነገር ....
እንደሌለና እንዲያውም ወደ ትዳሯ እንድትመለስ ትገፋፋት እንደነበረ ተናግራለች።ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና ግን ለፈተና ወራት የቀራት ፌኔት በአሠቃቂ ሁኔታ ህይወቷን አጣች።
ፖሊስም የምርመራ መዝገቡን በማስረጃና በአስክሬን ውጤት በማደራጀት አጠናቆ ለአቃቢ ሕግ ልኳል፡፡አቃቢ ሕግም በከባድ የሠው መግደል ወንጀል ክስ ይመሠርታል።
ክሱን የተመለከተው የኢሊባቡር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 26 ቀን 2018 በዋለዉ ችሎች ባልተረጋገጠና ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይኖረው ሟችን ትዳሬን ያፋታሽው አንቺ ነሽ በማለት የግድያ ወንጀል መፈፀሙ እጅግ ነውረኛ፣ ጨካኝና አደገኛ መሆኑ....
የሚሳይ ቢሆንም በሑለት የክስ ማቅለያዎች ፍርድ ቤቱ፣ በ21 ዓመት እስራት እንዲቀጣ የወሠነበት መሆኑ ምክትል ኢንስፔክተር አበራ አሠፋ ጨምረዉ ተናግረዋል። Via፦ ዳጉ ጆርና