
29/08/2025
" የአስራ አምስቱ ሰዎች አስክሬን ፍለጋ ቀጥሏል፤ ነገር ግን እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ" - የቡሌ ወረዳ አስተዳደር
በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ በተከሰተዉ የመሬት መንሸራተች አደጋ በትናትናዉ ዕለት የ17 ሰዎች አስክሬን አለመገኘቱን ዘግበን የነበረ ሲሆን ቲክቫህ ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት ቦታዉ ድረስ በማቅናት የአደጋው ሁኔታ ተመልክቷል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በአደጋዉ ስፍራ አግኝቶ ያነጋገራቸዉ የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሳ እንደገለፁት የአደጋው ዘግናኝነትና የመልካምድሩ አስቸጋሪነት የአስክሬን ፍለጋዉን አዳጋች ማድረጉን ተናግረዋል።
" ከትናንት እስከ ዛሬ በተደረገዉ ፍለጋ ከናዳዉ ስር አንድም አስክሬን ማዉጣት አልተቻለም " ያሉት ዋና አስተዳዳሪዉ " የአንዲት ታዳጊ አስክሬን በወራጅ ዉሃ ተወስዶ ከናዳዉ በቅርብ ርቀት ተገኝቷል " ሲሉ አስታውቀዋል።
በማሽን የታገዘ ፍለጋ ለማካሄድ ቦታዉ ተሽከርካሪ ለማስገባት እጅግ አደጋች ከመሆኑም በላይ በአከባቢው የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በሰዉ ሃይል ቁፋሮ ለማካሄድም ከአቅም በላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ዛሬ የአከባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ርብርብ የአንዲት ታዳጊ አስክሬን ከአደጋው ስፍራ የአንድ ወጣት አስክሬን ደግሞ ዉሃ ወስዶት ከነበረበት ከናዳዉ በቅርብ ርቀት ማግኘት መቻሉንም አቶ በራቆ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
በአከባቢው በከፍተኛ ስጋት ዉስጥ ካሉ አከባቢዎች እንዲሁም ከአደጋው ለተረፉ ዘጎች መጠለያና ሰብዓዊ ድጋፍ የማዳረሱ ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
ሀዋሳ