
04/09/2025
ለህዝብ ያለንን ክብር ተገቢ አገልግሎት በመስጠት ማረጋገጥ ይገባል፦አቶ ለንደቦ አወኖ
የሀዲያ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ለህዝብ በሚሰጠዉ አገልግሎት ዙሪያ ያተኮረ መድረክ አካሂዷል።
(ነሐሴ 28/2017 ሆሳዕና
በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ለንደቦ አዎኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት፦እንደ ዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የሕዝብ እንቅስቃሴና አጠቃላይ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።
ለዚህ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታየዉ አካላት ጋር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንዳለ አንስተዉ፥በተለይ ወረዳዎችን ከሆሳዕና ከተማ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ተሰርተዉ ለህዝቡ ተገቢ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የክልሉ ገጠር መንገዶች በበጋ ወቅት እንዲሰሩልን ሀሳብ እያቀረብንና በቅንጅት እየተሰረን እንገኛለን ብለዋል።
እንደዞናችን አሁን ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ ለህዝቡ የሚንሰጠዉን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ ተቋሙ፣መነሃሪያ ዉስጥ ያሉ ማህበራት፣ባለንብረቶችና የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የገለፁት የመምሪያዉ ኃላፊ አቶ ለንደቦ አዎኖ፥
ለህዝብ ያለንን ክብር ተገቢ አገልግሎት በመስጠት ማረጋገጥ ይገባል ብለዉ፥ የሚንሰጠዉን አገልግሎት በማጓደል ሕዝብን በመበደል የሚመጣዉ መዘዝ መንግስት ከሚጠይቀን በላይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመቀ በዶሬ እንደሚሉት፦በዞኑ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስታወሉ ጉድለቶችን ለመፍታትና ለህዝቡ ጤናማ አገልግሎት ለመስጠት፥ሁለት ችግሮች መፈታት አለባቸዉ ብለዋል።
የመጀመሪያዉና ዋናዉ መስተካከል ያለበት መነሃሪያዎች ዉስጥ ያሉ የመንግስት መዋቅሮችና ማህበራት ጤናማ አገልግሎት እንዲሰጡ በተቀናጀ መንገድ መስራት ሲሆን ሌለኛዉ ደግሞ ከመነሃሪያ ዉጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በትራፊክ ፖሊሶችና በመንገድ ዳህንነት ተቆጣጣሪዎች ዓማካይነት ጠንካራ ቁጥጥር በማድረግ ህግን የማስከበር ስራ መስራት ከተቻለ ለህዝቡ ተመጣጣኝና ችግር ፈቺ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ የክልሉ ርዕሰ-መዲና መሆንዋን ተከትሎ በርካታ ኩነቶች የሚከወኑበት ከተማ በመሆኑ እናም ከፊታችን ብዙ የሚናከብራቸዉ ህዝባዊ በዓላት በመኖራቸዉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡ የከተማዉን ፀጥታ መረበሽ ስለማይገባ የሚመለከታቸዉ ተቋማት ከወዲሁ ያሉትን ማነቆዎች ለይተዉ በመፍታትና እንዲያስተካክሉ አሳስበዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ በሰጡት አስተያዬት፦በከተማችን የሚንሰጠዉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳይ ለሚንሰራቸዉ የልማት ስራዎችና ለከተማዉ ኢኮኖሚ መነቃቃት አጋዥ እንጂ፡የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መሆን እንደሌለበት አንስተዋል።
በከተማዉ ያሉት ሁለቱ መነሃሪያዎች ተጥረዉና የንብረት ዳህንነት ተጠብቆ ለተገልጋዪ ማህበረሰብ የሚሰጡ አገልግሎቶች በተቀመጠላቸዉ የአሰራር ስርዓት መሰረት መሆን ይገባል ያሉት ከንቲባዉ አቶ ዳዊት ጡምደዶ፥
ከተማችን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ እንደመሆኑ መጠን በርካታ እንግዶችን የሚያስተናግድ በመሆኑ እንዲሁም ተጨማሪ እንደ እምግሬሺን፣ወሳኝ ኩነት፣የሰላምና ፀጥታና ፋይናንስ ቢሮዎች በከተማችን በመሆናቸዉ አገልግሎት በመፈለግ ከሌላ አካባቢዎች የሚመላለሱ ዜጎች ፍትሃዊ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ተጨማሪ ስራ እንደሚጠይቅ አንስተዉ፥
በዘርፉ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች በማጠናከር፥የሚስታወሉ ጉድለቶች እንደ ከተማ መዋቅር አይተን በማረም የሚሰዉ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ህደት እንዲዘምን፣ፍትሃዊ እንሆንና በወቅቱ ያለዉን የተገልጋይ ማህበረሰብ ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ኤርቆጮ በበኩላቸዉ፥በሆሳዕና ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዩን ፍላጎት በሚመጥን ደረጀ እንዲደርስ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ህዝባችን በሰላም ከቦታ ወደ ቦታ ዳህንነቱ ተጠብቆ እንድንቀሳቀስ በበኩላችን ብዙ ጥረት እየተደረገ ነዉ ብለዉ፥ነገር ግን አሁንም ያልተፈቱና ተጨማሪ ስራ የሚጠይቁ ነገሮች መኖራቸዉን አንስተዉ፥ እነዚህን ጉዳዮች ለመፍታትና ለህዝባችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ከአቅማችን በላይ በመሆናቸዉ የሚንቸገርባቸዉ ነገሮች አሉ ብለዋል።
ለአብነት ከወረዳዎች ጋር የሚያስተሳስሩን መንገዶች በተለይም ከግቤ፣ከምሻ፣ከዱናና ዋስገበታ ጋር የሚደረጉ ምልልሶች ወደ መቋረጥ ደረጀ ደርሰዋል ያሉት አቶ ተሾመ ኤርቆጮ፥ ተሽከርካሪዎች ወደእነዚህ አካባቢዎች ሄደዉ በሰላም እየተመላለሱአገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ሁኔታ እንደሌላየ ተናግረዉ፥የሚመለከተዉ አካል እነዚህን ጉዳዮች በትኩረት አይቶ ብፈታልን ለተገልጋዮቻችን ተገቢ አገልግሎት እንሰጣለን ብለዋል።
በሌላ በኩል በእነዚህ መንገዶች መበላሸት ምክንያት በሰዉም በንበረትም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እኛ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ከሚመለከታየዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተን ለመስራት ቁርጠኛ ነንም ብለዋል አቶ ተሾመ።
ለህዝብ የሚንሰጠዉ አገልግሎት በህገወጥ መንገድ በመንቀሳቀስ በተንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ማለትም የተሰጣቸዉን መርሃ ግብር የጣሱትን፣ከታሪፍ በላይ ያስከፈሉትንና ትርፍ የጫኑትን ብዙ ተሽከርካሪዎች ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃዎችን መዉሰድ እንደተቻለ የተናገሩት አቶ ተሾመ፥
የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲባል ይህ ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሆሳዕና ከተማ መነሃሪያ በጉዳዩ ዙሪያ አግኝተን ያነጋገርናቸዉ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በበኩላቸዉ፤ከወረዳዎቾ የሚመጡ ተገልጋዮች በመንገድ ብልሽት ምክንያት እንደሚጉላሉ አንስተዉ የሚመለከተዉ አካል ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
ማንኛዉም ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ መኪና ከመነሃሪያ ዉጭ በማደር በመንግስትና በህዝብ ጥረት እየተገነቡ ባለዉ የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፥መነኻሪያ ዉስጥ አድሮ ስምሪት በመዉሰድ ስራዉን መስራት እንደሚገባም በመድረኩ ተነስቷል።
በዉይይቱ መርሃ ግብር የዞንና የሆሳዕና ከተማ የሰላምና ፀጥታ፣የትራንስፖርት፣ የፖሊስና የትራፊክ ፖሊስ አመራሮችና የሚመለከታቸዉ ባለሙያዎች እንዲሁም የሆሳዕና መነሃሪያ የማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በኤልያስ ተሰማ