
19/04/2025
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ የ2017 የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ፤
ውድ የክፍለ ከተማችን ነዋሪዎች እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሰን፣ አደረሳችሁ !!
በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ሥፍራ ተሰጥቷቸው ከሚከበሩ በዓላት መካከል በዓለ ትንሣኤው በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የፍቅር ጥግ የታየበት ፣ የዕርቅና የይቅርታ ትርጉም የተገለጠበት ፣ ምሕረትና ድኅነት የተረጋገጠበት ፣ የአዳም ተስፋ የተፈፀመበት ታላቅ በዓል ነው።
በቀዳሚዎቹ ዘመናት አባታችን አዳም አትብላ የተባለውን ዕጸ በለስ በልቶ የፈጣሪን ትእዛዝ ከተላለፈ በኋላ የሰው ልጅ የአምላክ ፍቅር ርቆት የፍዳ ዘመናትን አሳልፏል።
በዲያቢሎስ ሤራ የተቆረጠው የፈጣሪና የፍጡር ፍቅር ዳግም እንዲታደስ አምላክ ከዙፋኑ ወደ ምድር ወረደ፤ በሰው ቁመትና ወርድ ተወሰነ፤ በደሙ አጥቦ የሰው ልጅን ከዘላለም ርግማን ሊያነፃ ክርስቶስ ታመመ፤ ስድብና ማንጓጠጡን ፣ ውንጀላና ግርፋቱን ፣ የዓለምን መከራ ሁሉ ያለ በደሉ ተቀበለ። ፍቅር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ታየ። ፍፁም ፍቅር ከክብር ዙፋን ላይ መውረድን እንደሚጠይቅ፤ እውነተኛ መውደድ በቅድመ ሁኔታዎች እንደማይታጠር ክርስቶስ በተግባር አስተምሮናል።
እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ ሁሉ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን፣ የኢትዮጵያችን ትንሣኤ እንደሚሳካ ምንም ጥርጥር የለውም።
የብልፅግና ጉዞ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የህብረት ጉዞ እንጂ ጥቂቶች የሚያሸንፉበት የጥሎ ማለፍ ሩጫ አይደለም። ስለሆነም በትብብር ፋንታ መጓተትን፣ በመደጋገፍ ፋንታ መገፋፋትን ከመረጥን ጉዟችን አንድ ርምጃ ወደፊት መቶ ርምጃ ወደኋላ ስለሚሆን ካሰብንበት ግብ በፍጥነት እንደርሳለን ማለት ዘበት ነው። ትንሣኤው አይቀሬ ነው። ፈተናው ተሸናፊ ነው። የጸናም አሸናፊ ይሆናል።
በድጋሜ መልካም የትንሣኤ በዓል!
አቶ ወልዴ ወገሴ ናኦ
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ
ሚያዚያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም