
21/08/2025
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው መማር ህገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን መወሰኑ ተገለፀ!
- ሀሩን ሚዲያ፥ ነሐሴ 15/2017
በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን የአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባችሁን ካላወለቃችሁ አትማሩም በሚል ከትምህርት ገበታ የታገዱት በያዝነው አመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር።
ተማሪዎቹ በዚህ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና እንዲሁም የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና እንዳይፈተኑ ተደርገዋል።
በተማሪዎችን ጉዳይ ጠበቃ ይዞ ከዞን ጀምሮ እስከ ክልል ሲከራከር የቆየው የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ውሳኔ ማግኘቱ ተገልጿል።
በዚህ መሰረትም የአክሱም ከተማ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ ሒጃብ አድርጎ መማር ህገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን በውሳኔው አሳውቋል።
ለአንድ አመት ያህል ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑት ተማሪዎች ያለፋቸው ትምህርት እና ብሄራዊ ፈተና በምን መልኩ እንደሚካካስም ሆነ ተማሪዎቹ በነበሩበት የክፍል ደረጃ ስለመቀጠላቸው የተባለ ነገር አለመኖሩ ተገልጿል።
© ሀሩን ሚዲያ