19/03/2026
ሼር
📍 "አይቻልም" ተብሎ ነበር! እዚህ ጋር ተቻለ
/ አቤል ብርሀኑ (የወይኗ ልጅ) /
ቀላል አልነበረም የሰው ልጅ እንደ ወፍ መብረር አይችልም ተብሎ በሳይንስ የታወጀበት ዘመን ነበር። እንዲያውም በወቅቱ ታዋቂ የነበሩት ካናዳዊ-አሜሪካዊው የስነ-ፈለክ ተመራማሪና የሂሳብ ሊቅ ሲሞን ኒውኮምብ (Simon Newcomb) "ከአየር የሚከብድ ማሽን መብረር አይችልም" ሲሉ አወጁ እንደ እሳቸው ያሉ ብዙ የዘመኑ ሳይንቲስቶችም ይህንን ሃሳብ እንደ ትልቅ ሳይንሳዊ እውነት አጽድቀውት ነበር።
ነገር ግን አለምን የለወጠው ግኝት የተገኘው ከዩኒቨርሲቲ ላብራቶሪዎች ወይም ከታወቁ ሳይንቲስቶች አልነበረም። ታሪክን የቀየሩት የሀይስኩል ትምህርታቸውን እንኳን ያላጠናቀቁት እና በሙያቸው የብስክሌት ጠጋኝ (Bicycle mechanics) የነበሩት ኦርቪል እና ዊልበር ራይት ነበሩ።
ዛሬ የቆምኩት ከልጅነቴ ስሰማው በጣም የሚያነቃቃኝ ታሪክ የተፈፀመበት የአሜሪካዋ ሰሜን ካሮላይና ኪቲ ሃውክ (Kitty Hawk) በሚገኘው የራይት ወንድማማቾች ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን የሞከሩበት ቦታ ነው ከጎኔ የምታዩት ምልክት የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራውን ያከናወነበትና "አይቻልም" የሚለውን የሊቃውንቱን ንግግር ውድቅ ያደረገበት ትክክለኛ ቦታ ነው።
እነዚህ የብስክሌት ጠጋኞች ወደዚህ ስኬት ለመድረስ ከ1,000 በላይ ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርገዋል። በሳይንሱ አለም ትልቅ ስም ባይኖራቸውም በውስጣቸው ግን የማይበገር ፅናት ነበራቸው። ብዙ ጊዜ ወድቀዋል ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን አሳልፈዋል ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ሁሉ ሰውተዋል። ነገር ግን እያንዳንዱ ውድቀት ለስኬታቸው እንደ አንድ ትልቅ ትምህርት ሆኖ አገልግሏቸዋል።
በመጨረሻም በታህሳስ 17፣ 1903 ዓ.ም. ያ የማይቻለው ነገር ተቻለ! ከፍተኛ ዲግሪ ያላቸው ሳይንቲስቶች "አይቻልም" ያሉትን ነገር እነዚያ የብስክሌት ጠጋኞች በፅናት እውን አደረጉት። ለመጀመሪያ ጊዜ የ12 ሰከንድ በረራ አደረጉ ያ በረራ የሰው ልጅን የታሪክ መስመር ለዘላለም ቀየረችው።
ትልቅ ህልም ካለህ እንኳን የቅርብህ ሰው አለም በሙሉ አይሆንም ሊልህ ይችላል በሺህ የሚቆጠሩ ሙከራዎችህ ሳይሳኩ ሊቀሩ ይችላሉ። ታላላቅ ስኬቶች የሚመዘገቡት በሰውን ንግግር እና መስማማት ሳይሆን የራሳቸውን ህልም በሚያዳምጡና "አይቻልም" የሚለውን ቃል በማይቀበሉ ፅኑ ሰዎች ነው። ህልምህን አትናቀው !!
ለምትወዱት ሰው ሼር አድርጉት !!