07/04/2026
ኢቢሲ ገዥ ትርክቶችን በማስረጽና የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት ረገድ የሚደነቅ ሥራ እየሠራ ነው፡- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
****
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ገዥ ትርክቶችን ለማስረጽና የኢትዮጵያን ከፍታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የሚደነቅ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር አብሮ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ በጽሕፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ኢቢሲ ገዥ ትርክቶችን ለማስረጽና የኢትዮጵያን ከፍታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የሚደነቅ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሕዝቦች አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከርና በልማት ኮሪደሮች የሕብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲያድግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አመልክተዋል።
ክልሉ ያለውን እምቅ የልማት አቅምና የተፈጥሮ ጸጋ ለዓለም ለማስተዋወቅ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙክታር ሁሴን በበኩላቸው፤ ተቋሙ የጀመራቸውን የሀገር ግንባታ ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልና የታርጫ ስቱዲዮን በግብዓት ለማሟላት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘላለም እንዳሻው በበኩላቸው፤ የክልሉን የልማት አቅሞች ከማስተዋወቅ ባለፈ የሚዲያ ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የኢቢሲ ከፍተኛ አመራሮች ከክልሉ አመራር ጋር ያደረጉት ውይይት የክልሉን የሥራ እንቅስቃሴዎችና ተግባራት ለማስተዋወቅና ሕዝቡ ወቅታዊና እውነተኛ መረጃን እንዲያገኝ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በሰለሞን ባረና