
24/03/2025
" በአንድ ቀን እናቴንና ነፍሰ ጡር ባለቤቴን ያሳጣኝ ባለሥልጣን እስር ቤት መሆኑን እንጂ መለቀቁን አላዉቅም ነበር " - ሚስትና እናቱን በአንዴ ያጣ ግለሰብ
" ግለሰቡ ከእስር ቤት ወጥቷል፤ ዉሳኔዉ ተገቢ ያልሆነና ከፍተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የታየበት ነዉ ! " - የሕግ ባለሙያዎች
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ሚጁ ታህሳስ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ስልጣንን ያለ አግባብ በመገልገል ያለመንጃ ፈቃድ የመንግስትን መኪና ለልምምድ በሚል ሲያሽከረክሩ በወረዳዉ አፉርሲ ተብሎ በሚጠራዉ አከባቢ በሰርግ መርሃግብር ላይ የነበሩ ሰዎች ላይ አደጋ አድርሰዋል።
በዚህም አንዲት ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ 2 ሰዎች ሞተዋል ፤ በ28 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት በባለስልጣኑ ደርሷል።
ባለስልጣኑ የጌዲኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዉ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሏቸው የ13 ዓመት ፅኑ እስራትና 10 ሺህ ብር ቅጣት ብይን ከሰጠ በኋላ የቅጣት ዉሳኔዉን ወደ 3 ዓመት ከ7 ወር ማዉረዱንና በ2 ዓመት ገደብ እንዲፀና በማድረግ ከእስር እንዲፈቱ ማድረጉን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የጌዲኦ ዞን ፍትሕ አካላት መናገራቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ አስነብቧል።
በአንድ ቀን ወላጅ እናቱንና ነፍሰ ጡር ባለቤቱን ያጣዉ አቶ ኩራባቸዉ ኤደማ " ወላጅ እናቴን እና ነፍሰ ጡር ሚስቴን ማጣቴ ለእኔ መግለፅ ከምችለዉ በላይ መሪር ሀዘን ነዉ " ብለዋል።
" ደማቸዉ ሳይደርቅ ገና በሁለተኛ ወሩ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ያደረገዉ ባለስልጣን ከእስር ቤት ተለቆ ወደ ቤቱ መግባቱን ሰዎች ሲነግሩኝ በጣም አዝኛለሁ " ሲሉ ተናግረዋል።
" እኔ አሁን ወደ ፈጣሪ ከማልቀስ በስተቀር የምካሰስበት አቅምም ሆነ ባለስልጣን ዘመድ የለኝም " የሚሉት አቶ ኩራባቸዉ " ከባለቤቴና ወላጅ እናቴ ሞት በኋላ ያለሁበትን መከራ እጅጉን ከባድና ተንቀሳቅሼ መስራት ስላልቻልኩ ሶስት ልጆቻችንን፣ አዛውንት አባቴን መመገብ ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል " ብለዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ የመንግስት የስራ ኃላፊ የዞኑ መንግስት የበላይ አመራሮች ጣልቃ ገብነት አደጋው ከተከሰተበት ማግስት ጀምሮ ይስተዋል እንደነበር ተናግረዋል።
በወቅቱ ተጎጂዎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ የሟቾችን መቃብር በሲሚንቶ በማሰራትና ባለሥልጣኑ እንዳይታሰር በማድረግ ስራ ተጠምደው ነበር ብለዋል።
" ባለስልጣኑ ከታሰሩ በኋላም ለተወሰኑ ጊዜያት እስር ቤት ሆነዉ ለወረዳዉ አመራሮች የስራ መመሪያ ይሰጡ እንደነበር፣ አልፎ አልፎም ካቢኔ ጠርተዉ ይሰበስቡ እንደነበርም " ገልፀዋል።
አንድ የዞኑ ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ " የዞኑ ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ከጅምሩ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ተስፋዬ ሚጁ በቁጥጥር ስር እንዳይዉል ከማድረግና ክስ እንዳይከፈትበት በማስጠንቀቅም ጭምር የቀጠለ ነበር " ይላሉ።
" በዞኑ ዐቃቤ ሕጎች ፅኑ አቋም ክስ ተመስርቶባቸው በጌዲኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል የወንጀል ድርጊቱን እንደፈፀሙ በማመናቸው ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግንና የተከሳሹን የግራና ቀኝ ክርክር ከሰማ በኋላ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መነሻ ጥፋተኛ በማለት በእርከኑ መነሻ ቅጣት በ8 ዓመት ፅኑ እስራትና የ13 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ብይን ከሰጠ በኋላ ከሁለቱም ወገን የቅጣት አስተያየት እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ለዉሳኔ መጋቢት 5 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር " ሲሉ ገልፀዋል።
" ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸዉን የቅጣት ማክበጃዎች ያልተቀበለው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹ ያቀረቡት ሰባት የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶችን ተቀብሎ መጋቢት 05 ቀን 2017 ዓ/ም ከተጠቀሰ ስምንት (8 ) ዓመት ጽኑ እስራትና 13 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትን ወደ 3 ዓመት ከ7 ወርና 2 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በማዉረድ የቅጣት አወሳሰን መምሪያ 2/2006 በማይፈቅድ ሁኔታ ቅጣቱን ወደ ገደብ ያመጣበት አግባብ መሰረታዊ የህግ ስህተት የተፈጸመበትና የዞን ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት በግልፅ የታየበት ነዉ " ብለዋል።
እንደ ባለሞያው አስተያየት " 1ኛ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 543 (3) የእስራት ቅጣት ከ5-15 ዓመት ጽኑ እስራትና ከ10-15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጫ የሚል፣ 2ኛ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 559 (2) እና (3) የወንጀል ክስ ለጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ተደራራቢ የወንጀል ድርጊት በመሆኑ ተደራራቢ ክስ ቀርቦበት የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በህግ አግባብ በማየትና ከጉዳዩ ገለልተኛ በመሆን መወሰን ሲገባው በፖለቲካ ጫና ዉሳኔዉን ወደ ገደብ ዝቅ አድርጓል " ሲሉ ተናግረዋል።
የዐቃቤ ሕግ ቡድኑ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለመጠየቅ ቢወስንም በበላይ ኃላፊዎች በኩል አሁንም ጫናዎች መኖራቸዉንና ተጎጂዎች ትክክለኛዉን ፍትሕ እስኪያገኙ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታዉቀዋል።
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ ጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ፍቃዱ የእጅ ስልክ እንደደወለ ያስነበበው ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃዉን ለመስጠት የስራ ፈቃድ፣ ለመስሪያ ቤታቸው በአድራሻ የተፃፈ ደብዳቤ እና የሠራተኛው መታወቂያ ኮፒ ይዛቾሁ በአካል ካልመጣችሁ መረጃ አንሰጣችሁም መባሉን ጠቅሷል።
👇
የገደብ ቅጣት ከየትኛውም አይነት ወንጀል ራሳቸውን አቅበው፤ የትኛውም የወንጀል ድርጊት ላይ እንዳይገኙ የሚል ነው። የወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈው ቢገኙ ግን የታገደው የቅጣት ውሳኔ ተፈፃሚ ይሆናል።