
28/07/2024
በታጣቂዎች ታግተው የነበሩት የኢፌድሪ አየር ኃይል አዛዥ ወንድሞች ከወራት እገታ በኋላ ተለቀቁ
በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታግተው ቆይተው የነበሩ የኢፌድሪ አየር ኃይል አዛዥ ጀነራል ይልማ መርዳሳ ሁለት ወንድሞች ከወራት እገታ በኋላ ተለቀቁ።
ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዜናፕላስ እንደተናገሩት፤ ታግተው ከነበሩት ሁለት የጀነራሉ ወንድሞች መካከል አንዱ ከአንድ ወር በፊት የተለቀቀ ሲሆን ሌላኛው ወንድም ደግሞ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተለቋል።
ቦረና መርዳሳ ኛጳ እና በቀለ መርዳሳ ኛጳ ከሦስት ወራት በፊት ወሊሶ አካባቢ ከሚገኘው ከመኖሪያ መንደራቸው በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ነበር የታገቱት።
ጀነራሉ የታገቱባቸውን ወንድሞቻቸውን ለማስቀለቀቅ ገንዘብ ከመክፈላቸው በተጨማሪ፤ የእገታውን ኦፕሬሽን የመሩ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኮማንደር ቤተሰብ አባላትን አሳስረው እንደነበረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ተናግረዋል።
እንድ ምንጮች ከሆነ ቦረና መርዳሳ የተባሉት ታላቅ ወንድም ባለፈው ሳምንት የተላቀቁ ሲሆን በቀለ መርዳሳ ግን ከስድስት ሳምንታት በፊት ነበር የለቀቁት። በአጠቃላይ ለሁለቱን ግለሰቦች ነጻ ለማውጣት 4 ሚሊየን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ መከፈሉ ተገልጿል።
በመንግሥት ኃይሎች ቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተይዘው የነረቡት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ቤተሰቦች እንዲሁ ከእስር ተለቀዋል።
የእገታ ወንጀል በተበራከተበት የኦሮሚ ክልል ከተራው ዜጋ እስከ የመንግሥት ባለስልጣናት ቤተሰቦች የመታገት ዜና መስማት አዲስ ነገር አይደለም።
ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ ወላጅ አባት ከአምቦ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ታግተው በሽምግልና እና በክፍያ ተለቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ወላጆች በታጣቂዎች ታግተው እንደነበር የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር።
የጀነራል ይልማ መርዳሳ ወንድሞች እገታ
የጀነራል ይልማ መርዳሳ ወንድሞች ቦረና መርዳሳ እና በቀለ መርዳሳ ከመታገታቸው በፊት ደቡብ ምዕራሽ ሸዋ አመያ ወረዳ በምትገኘው መኖሪያ መንደራቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመንግሥት ኃይል ሰፍሮ ነበር።
ከሦስት ወራት በፊት ሚያዚያ 6/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት የአየር ኃይል አዛዡ ወንድሞች በሚኖሩበት መንደር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፈቱ።
ታጣቂዎቹ ትምህርት ቤት ላይ ሰፍሮ የነበረ የመንግሥት ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ የጀነራሉን ወንድሞች ለመያዝ ወደ መኖሪያ መንደራቸው አምርተው ነበር።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደሚሉት በዕለቱ በአንድ መንደር ይኖሩ ከነበሩት ሦስት የጀነራሉ ወንድሞች መካከል አንዱ ከታጣቂዎች ጋር ተታኩሶ ተገድሏል።
ቦረና እና በቀለ የተባሉት የይልማ መርዳሳ ታላቅ ወንድሞች ግን እጅ ሰጥተው በታጣቂዎቹ ታግተው ተወስደው ነበር።
የሁለቱን ወንድማማቾች እገታ ተከትሎ ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቅርበት ያላቸው የማሕበራዊ ገጾች ከታጋቾቹ ጋር የተገደረገ ቃለ መጠይቅ ቪዲዮ ማሕብራዊ ሚዲያ ላይ አውጥተዋል።
ሁለቱ ወንድማማቾች በቪዲዮ የሚናገሩት ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ስለ ቤተሰቡ እና እገታውን በተመለከተ ከተናገሩት ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሁለቱ ግለሶበች ቪዲዮ ምን ይላሉ
ዘለገ ባለው የቪዲዮ ቃለ ምልልስ ቦረና መርዳሳ ልጆችን ጨምሮ አጠቃላይ 23 የቤተሰብ አባላት በአንድ አካካቢ ተሰባስበው እንደሚኖሩ ይናገራሉ።
“እኛ ገበሬዎች ነን። የማሕብረሰብ አካል ነን። ከመንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኑነት የለንም” ይላሉ።
ቦረና የመንግሥት ሠራዊት አባላት ለጀነራሉ ቤተሰቦች ጥበቃ ለማድረግ የቤተሰብ አባለቱ በሚኖሩበት አካባቢ መስፈራቸውን ይናገራሉ።
ሁለቱ ወንድማማቾች ይህ ቃለ መጠይቅ የሰጡት በምን አይነት ጫና ውስጥ ሆነው እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም በቪዲዮ ላይ የሚናገሩት ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ከሰጡት አስተያየት ጋር የሚቃረን አይደለም።
“ለምን እንደመጡ (የመንግሥት ጦር) የምናውቀው ነገር የለም። ጥበቃ እንዲያደርጉልን አልጠየቅንም። . . . ለምን እንደተመደቡ እኛ ምንም አናውቅም። እኛ ትዕዛዝ መስጠት እንችልም። ይህ ጦር እዚህ መስፈሩ ለእኛ ምንም ፋይዳ የለውም ብለን ተናግረናል። ወድማችንንም አስጠይቀናል (ይልማ መርዳሳ) እሱም አጥጋቢ ምላሽ አልሰጠንም። ከማሕብረሰቡ ተለይተን እኛ እንደ የጦሩ አካል ነው የምንታየው። ሰው አይጠጋንም። ሰው ሞቶ ቀብር መሄድ እንችል። ከሰው ተለይተን ነው ስንኖር የኖርነው” በማለት ቦረና መርዳሳ ይናገራሉ።
ጀነራል ይልማ መርዳሳ ምንም እንኳ የአገሪቱ ከፍተኛ ጦር አዛዥ ቢሆኑም በወንድም ደረጃ የሚገኙ የቅርብ ዘመዶች በበግብርና በእጅ ሙያ እየሰሩ የሚተዳደሩ መሆናቸውን ለቤተሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ።
የግለሰቦቹን እገታ በተመለከተ ከታጣቂ ቡድኑም ሆነ ከአየር ኃይሉ አዛዥ አስተያየት ለመቀበል ያደረግነው ጥረት መልስ አላገኘም።