
21/08/2024
የ95 ዓመቱ ኬንያዊ አዛውንት የ90 ዓመት ሚስት ማግባታቸው አነጋጋሪ ሆኗል
የእውነተኛ ፍቅር ፅናት በሚል በተደገሰው የሰርግ ስነስርዓት ላይ የ95 ዓመቱ ኢብራሂም ምቦጎ እና የ90 ዓመቷ ታቢታ ዋንጉይ ባሳለፍነው እሁድ እኤአ ነሐሴ 18 ቀን በሚያምር የሰርግ ስነስርዓት ላይ በይፋ ቀሪ ዘመናቸውን አብረው ለማሳለፍ ቃል ተገባብተው ባልና ሚስት ተብለዋል።
ከስድስት አስርት አመታት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ የተዋወቁት ኬንያውያን ጥንዶች በአስደናቂው የቤተክርስትያን ስነስርዓት ላይ ስእለት ሲለዋወጡ ታዳሚው ሁሉ በደስታ ተሞልቶ ነበር። ይሄው ልብ የሚነካ ህብረታቸውም ሰሞኑን የሀገሪቱ በዜጎች ዲጂታል መገናኛ ዘዴዎች ላይ ሲቀባበሉት ሰምብተዋል።
በ1960 ተገናኘንና ተዋደድን ፣ ከዛ በኃላ ያለው ታሪክ ነው ሲልም ምቦጎ ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በስተሰሜን ምስራቅ የሶስት ሰአት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ ባለቺው ሙኩርወይኒ ውስጥ በምትገኘው ቤተክርስትያን ውስጥ ሲናገር ተደምጧል።
"አንድ ላይ ተወያይተን ይፋዊ ሰርግ ብናደርግ ጥሩ እንደሚሆን ተስማማን፣ በኪኩዩ ባህላችን መሰረት ከዚህ ቀደም በህጋዊ መንገድ ተጋብተናል፣ ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች በመሆናችን የቤተ ክርስቲያን ሰርግ ለማድረግ ወሰንን" በማለት በ95ና90 ዓመታቸው ሰርግ ለመደገስ የወሰኑበት ምክንያት ያብራራሉ።
ሙሽራው ለልዩ ቀናቸው በልካቸው የተሰፋ ግራጫ ቀለም ያለው ሱፍ እንዲሁም የብር ቀለም ያለው ክራባት የለበሰ ሲሆን፣ ሙሽራዋ ደግሞ ነጭ ኮፍያ ክሬም ቀለም ያለው ጃኬት በነጭ ልብሷ ላይ ጣል አድርጋ ነበር።
ረዥም ዘመን ስላስቆጠረው ጥምረታቸው ሚስጢር የተጠየቀቺው ዋንጊ ለሲቲዝን ዲጂታል በሰጠቺው መልስ “ሴቶች፣ ባሎቻችሁን ማክበር አለባችሁ፣ ያንን ካደረጋችሁ፣ እንደኛ ረዥም ዘመን በትዳር ትኖራላችሁ ሰትልም ተደምጣለች።
"ምንም አትበድል፣ ጥፋት ስትሰራ ደግሞ ይቅርታ ጠይቅ እና ይቅርታም አድርግ" የሚሉት ደግሞ የህይወታቸው መርሆች ረዥም ዘመን ላስቆጠረው ትዳራቸው ደግሞ የጀርባ አጥንት እንደነበሩም ገልፀዋል።