
03/10/2025
ባለፈው አንድ ዓመት "ኢኮኖሚያዊ አሻጥርን ጨምሮ ህገወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፈዋል" የተባሉ 39 ሺህ ሰነድ አልባ የውጭ ዜጎች መያዛቸው ተገለፀ
ባለፈው አንድ ዓመት 39 ሺህ የውጭ ዜጎች በሕገ-ወጥ ሰነድ ሲገለገሉ መያዛቸውን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ። እነዚህ ግለሰቦች "ኢኮኖሚያዊ አሻጥርን ጨምሮ በህገወጥ ክንውኖች ውስጥ ሲሳተፉ የተገኙ ናቸው" ብሏል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ ማንኛውም ዜጋ ሕጋዊ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲኖረው ይገደዳል ሲሉ ገልፀዋል።
ሕጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱ የውጭ ዜጎች በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ፣ ጸጥታ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ የገለፁት አቶ ጎሳ ይህንን ለመከላከልም ባለፈው 2017 በጀት ዓመት ብቻ 39 ሺህ ሰነድ አልባ የውጭ ዜጎችን መያዝ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
የተያዙት ሰነድ አልባ ሰዎችም "በኢኮኖሚ ላይ አሻጥርን የሚያከናውኑ፣ ሕገ ወጥ ማኅበራዊ ክንውን ላይ የተሰማሩ እና የኢትዮጵያን ደኅንነት በሚጎዱ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ናቸው" ብለዋል።
አግባብነት የሌላቸው ሰነዶችን የሚጠቀሙበት ምክንያትም "ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማሳካት፣ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ከግብ ለማድረስ፣ የሚሠሩት ሥራ እና እንቅስቃሴያቸው እንዳይታወቅ ከመፈለግ የመጣ እንደኾነም" ጠቁመዋል።
አያይዘውም እነዚህ ጉዳቶች ያለሰነድ እና ፍቃድ ሲከናወኑ ደግሞ በሀገሪቱ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በመኾኑ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው አሚኮ ነው።