14/08/2026
ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው? 35 ዓመት የክልሉ መቀመጫ አልነበረችም ወይ!
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ አዲስ አበባንና የኦሮሚያ ክልልን በተመለከተ አዳዲስና የሚያስፈሩ ትርክቶች ሆን ተብለው ሲፈበረኩ እንሰማለን። ግን እስቲ ቆም ብለን በምክንያት እናስብ፤ ዛሬ የተለየ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው? አዲስ አበባ ላለፉት 35 ዓመታት የኦሮሚያ ክልል መንግስት መቀመጫ ሆና አላገለገለችም ወይ?
በእነዚህ 35 ዓመታት ውስጥ ከተማዋ የፌዴራል መንግስቱ ርዕሰ መዲና፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሰላም፣ በፍቅርና በአብሮነት የሚኖሩባት "ትንሿ ኢትዮጵያ" ሆና ዘልቃለች። በተጓዳኝ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ማዕከል በመሆኗ የተፈጠረ አንዳችም የጎላ ችግር አልነበረም። ይልቁንም ይህ ሁኔታ አብሮ ለማደግና ሰላምን ለማስፈን ትልቅ ዕድል የፈጠረ ነው።
ከተፈጥሯዊ ማህጸኗ ኦሮሚያ ጋር ያላት ጥብቅ ቁርኝት ትናንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ነገም የሚቀጥል ፀጋ እንጂ ስጋት ሊሆን አይችልም። "ልዩ ጥቅም" በሚለው የሕገ-መንግስት ቃል ፈንታ "የጋራ ተጠቃሚነት" የሚል ማዕቀፍ መዘጋጀቱ የ35 ዓመቱን ጤናማ አብሮነት ሕጋዊና ዘመናዊ ከማድረግ የዘለለ ምንም የተለየ አጀንዳ የለውም። ስለዚህ የፈጠራ ስጋቶችን ትተን የሁላችንም በሆነችው አዲስ አበባ የጋራ ብልጽግና ላይ ብቻ እናተኩር!