
31/07/2025
የአንጋፋው አቃቤ እምነት ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ የሦስት አስርት ዓመታት የአገልግሎት አበርክቶ እውቅና መስጫ መርሃ ግብር በአትላንታ ከተማ ተካሄደ፡፡
በዚህ ጁላይ 27/2025 በአትላንታ ርኆቦት የኢትዮጵያውያን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በተካሄደ መርሃ ግብር ላይ በከተማዋ የሚገኙ እና ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የመጡ የዶ/ር ተሰፋዬ አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ የቤተ ክርስቲያናት መጋቢያን እና መሪዎች፣ እንዲሁም ቤተሰቦቹ እና ወዳጆቹ በመገኘት ለአገልጋዩ አክብሮታቸውን የገለጹ ሲሆን ደጋፊ በማጣት እየተዳከመ የመጣውን የእቅበተ እምነት አገልግሎቱን በጽናት እንዲቀጥልም አበረታተውታል ተብሏል፡፡
በተካሄደው የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም ላይም ከአዲስ አበባ እነ ጋሽ ንጉሤ ቡልቻን የመሳሰሉ አንጋፋ አገልጋዮች እንዲሁም በዶ/ር ተስፋዬ አገልግሎት ከተለያዩ የስህተት ትምህርት አስተማሪ ቤተ እምነቶች ወጥተው በወንጌል አማኝ ቤተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ አገልጋዮች እና አማኞች ስለ ዶ/ር ተስፋዬ እና የሚሰጠው አገልግሎት ጠቀሜታ የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ መገኘት የቻሉ የተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት መጋቢያን እና አገልጋዮችም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በከፋ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን የተለያዩ የኑፋቄ አስተምህሮዎችን የሚያጋልጡ እና ቤተክርስቲያንን በዚህ ዙሪያ ተዘጋጅታ እንድትቆም በማስታጠቅ አገልግሎት የተሰማሩ እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ ያሉ አገልጋዮችን መደገፍ አማራጭ የሌለው አደራዋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡