
30/10/2024
⭕️ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ጥቅምት 20/2017 ዓ፣ም ዕለታዊ ዜናዎች
1፤ የሱማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ዓሊ ሞሐመድ አደን የተባሉ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ዲፕሎማት በ72 ሰዓታት ከአገሪቱ እንዲወጡ ትናንት አዟል።
ሚንስቴሩ፣ ዲፕሎማቱ ከዲፕሎማሲ ተልዕኳቸው ጋር አብሮ የማይሄድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር በማለት ከሷል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ በዲፕሎማቱ መባረር ዙሪያ ያለው ነገር የለም።
2. የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ "ተቀራርቦ መነጋገርን የመሰለ ነገር የለም" በማለት ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል በጋራ ከተነሱት ፎቶ ጋር በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጌታቸው፣ ከሩቅ የሚመጣ ሰው አያስፈልግም በማለት ኹለቱን የሕወሓት ቡድኖች ለማገናኘት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አካላትን አመስግነዋል። ጌታቸው ከደብረጺዮን ጋር በምን ጉዳዮች ላይ እንደተነጋገሩ፣ መቼና የት እንደተገናኙ ወይም የትኞቹ አካላት እንዳቀራረቧቸው ግን አልገለጡም።
3፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ካለፈው ስምንት አጋማሽ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ግንባሮች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር በተካሄዱ ግጭቶች 102 የመንግሥት ወታደሮችንና በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ማርኬያለኹ ሲል አዲስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አማጺው ቡድን በመንግሥት ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ድል ተቀዳጅቻለኹ ያለው፣ ድሬ ኢንጪኒ፣ ደራ፣ ወረ ጃርሶ፣ አመያ፣ ዩብዶ፣ ጉቴ፣ ቦጂ፣ ቡኖ በደሌ፣ ሳሲጋ፣ አባይ ጮመን፣ ሀርጡማ ፉርሴ፣ ኤልዋዬ፣ ገላና፣ ሱሮ ቡርጉዳ፣ በቾ እና ቦራ በተባሉ የግጭት ግንባሮች ነው። ቡድኑ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች፣ የግንኙነት መስመሮች እንደተቋረጡ መኾኑንም ጠቅሷል። መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ፣ በቡድኑ ላይ መጠነ ሰፊ የኃይል ርምጃ እየወሰደ መኾኑን ገልጧል።
4፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን መድረሱን አስታውቋል።
ባንኩ፣ በሩብ ዓመቱ ውስጥ 121 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱንም ገልጧል። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ባንኩ 640 ሚሊዮን የገንዘብ ዝውውር በዲጂታል አማራጮች መካሄዱንና ይህም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ46 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አውስቷል። በባንኩ የዲጂታል የክፍያ አማራጮች የ3 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ግብይት እንደተፈጸመም ተገልጣል። [ዋዜማ]