
29/01/2023
‹‹ደደብነት ያለማወቅ ችግር ሳይሆን የስብዕና መቃወስ፣ የሞራል ማጣት ነው››
(Stupid people are more dangerous than evil ones)
(እ.ብ.ይ.)
አለማወቅ ምንም አይደል፤ በማወቅ ይደመሳሳል፡፡ አለመማርም ችግር የለውም ቀለም በመቁጠር ድል ይነሳል፡፡ አለማወቅ መረጃ አለማግኘት ነው፡፡ አለመማር ስራዬ ብሎ የኑሮን ቀለም፣ የህይወትን ፊደል አለመቁጠር ነው፡፡ አለመማር ወደመረጃው ዓለም የሚወስደውን መንገድ አለመጀመር ነው፡፡ አለማወቅ አለማሰብ መቻል አይደለም፡፡ አለመማርም የሃሳብ እጦት ባለቤት መሆን አይደለም፡፡ የተማረውም ያልተማረውም ያስባል፤ ልዩነቱ የሚያስበው ነገር የተለያየ መሆኑ ነው፡፡ የተማረ ሁሉ በሃሳቡ የሰለጠነ ነው ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንድ ሰው በአለባበሱና በአበላሉ የሰለጠነ ይመስላል፤ በአስተሳሰቡ ግን ኋላ የቀረ ነው፡፡ መሰልጠን ፋሽን መከተል የሚመስለው አያል ነው፤ መዘመን የዘመኑን መረጃ ማነብነብ ብቻ የሚመስለው መዓት ነው፡፡ እውነተኛ ዘመናዊነት ግን ዓለሙ ያቀረበልህን መረጃና ዕውቀት መመዘን፣ ማጥናት፣ መተንተን፣ ጥቅምና ጉዳቱን መለየት፤ ደካማና ጠንካራ ጎኑን ማውጣት፣ እንዲሁም የራስን ሃሳብ አክሎ አዲስ በጎ አተያይ መፍጠር መቻል ነው፡፡ ዘመናዊነት ዘመኑ የደረሰበት የአስተሳሰብ ወለል ላይ መድረስ ነው፡፡ መሰልጠን ግን ዘመኑን መቅደምም ሊሆን ይችላል፡፡ የሰለጠኑ ሐገራት ሰለጠኑ የሚባሉት በጊዜው የነበራቸውን ችግር ስለቀረፉ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶቻቸውን ቀድመው አውቀው ለእሱ መፍትሄ ማበጀት በመቻላቸው ነው፡፡
ሰው ሁሌም የሕይወት ተማሪ ነው፡፡ ከጥፋቱ የሚማር፣ ከሌሎች ውድቀትና ስኬት ቀለም የሚቆጥር፣ በመደበኛ ትምህርት ራሱን የሚገነባ ሰው ብልህ ሰው ነው፡፡ ሰው አስተዋይ ከሆነ በዕድሜው ከሚያየው ያውቃል፤ ከሚሰማውም ይማራል፡፡ ሰው አዋቂ ሆኖ፣ ፊደል ቆጥሮ፣ ቀለም ለይቶ፣ የትተረፈረፈ መረጃ ኖሮት፣ በትምህርቱ ዓለም ብዙ ተጉዞ፣ ስምና ዝና፤ ሃይልና ስልጣን ይዞ ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ ማመዛዘን፣ ማስተዋል ካልቻለ ግን ደደብነት ይወርሰዋል፡፡ ድድብና አዕምሮንም ልብንም መጠቀም አለመቻል ነው፡፡ ሰው በዓይኑ ያየውን፣ በጆሮው የሰማውን፣ ከዚህ ቀደም በንባብ ያወቀውን፣ በጥናት የደረሰበትን ሃሳብና ዕውቀት በልቡ አመላልሶ፣ በሕሊናው አብላልቶ፣ ክፉና ደጉን ለይቶ በሰናይ ተግባር ላይ ካላዋለው፤ በጎ ውሳኔ ላይ ካላደረሰው እሱ ያልተማረ ሳይሆን የተማረ ደደብ ነው ማለት ነው፡፡ ደደብነት የሚገፈፈው በመንፈሳዊ ዕውቀት ሲሰለጥኑ፣ በሰውነት ሲዘምኑ፣ ስሜትን ሲገሩ፣ ለሐገር ለወገን የሚጠቅም ችግር ፈቺ ሃሳብ አስበው ሲተገብሩ ነው፡፡
የዚህ ዘመን ትልቁ ችግር ያልተማሩ ሰዎች ቁጥር መበራከቱ ሳይሆን አዋቂ የተባሉ፣ የተማሩ መሃይማን እጅግ እየበዙ መምጣታቸው ነው፡፡ የክፉ ሰዎች ክፋት ሳይሆን የደደቦች ጥፋት ነው ሐገራችንን የሞት አፋፍ ላይ ያቆማት፡፡ ክፉዎችን መከላከል ትችላለህ፤ ደደቦችን ግን አትችልም፡፡ ደደቦችን በመልክ ለይተህ አታውቃቸውም፡፡ ከቤተሰብህ፣ ከጓደኞችህ፣ ከባልንጀሮችህ፣ ከመምህራኖችህ፣ ከሃይማኖት አባቶችህ፣ ሐገርህን ከሚመሩት ባለስልጣኖችህ መካከል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ክፉዎችን በአነጋገራቸው፣ በአስተያየታቸው፣ አንዳንዴም በዓይናቸው ልታውቃቸው ትችላለህ፡፡ ክፉዎች ትንሽም ቢሆን አጥንተው ነው ሊያጠቁህ የሚፈልጉት፡፡ ደደቦች ግን ‹‹የፈሪ ብትር ሆድ ይቀትር›› እንዲል ቢሂሉ ጥፋታቸው ደመነፍሳዊ ነው፡፡ አዎ ደደቦችን አደጋ ካደረሱ በኋላ ነው የምታውቃቸው፡፡
ጀርመናዊው የስነመለኮት ሊቅ የነበረው ዳያትሪክ ቦንኹፈር (Dietrich Bonhoeffer) በሃያኛው ክፍለዘመን በጀርመን የጨለማ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ጀርመን በህዝብ ተቃውሞ ስትናጥና ተቃዋሚዎች የንፁሃንን ንብረትና የንግድ ሱቆች በድንጋይ ሲሰባብሩ ዓይቶ ፊትለፊት በአደባባይ የሕዝብን ድርጊት ያወገዘ ሰው ነበር፡፡ በኋላም ሒትለርን ለማስገደል ካሴሩት ሰዎች አንደኛው ነህ ተብሎ ተከስሶ እ.ኤ.አ. በወርሃ ሚያዚያ 1945 ዓ.ም. በስቅላት የተቀጣ ሰው ነው፡፡ ይሄ የሉተራን ቤተክርስቲያን ፓስተር የነበረ ሰው ‹‹የደደብነት ንድፈ ሃሳብ (Theory of Stupidity)›› በሚል ሃሳቡ ይታወቃል፡፡ ‹‹ደደብ ሰዎች ከክፉ ሰዎች የበለጠ አደገኞች ናቸው›› ይላል፡፡ ይሄንንም ሲያብራራ ‹‹ክፉ ሰዎችን ፊትለፊት ሃይል በመጠቀም መከላከል ይቻላል፤ ደደቦችን ግን ለመከላከል አቅመቢስ እንሆናለን፡፡ ምክንያቱም ጆሯቸው ምክንያታዊነትን ላለመስማት ደንቁራል፡፡›› ይለናል፡፡ ሰውየው በዚህ አላበቃም፡፡ ‹‹ደደብነት ያለማወቅ ችግር ሳይሆን የሞራል ማጣት ነው›› ‹ብዙ ምሁራን አሉ ነገር ግን ደደቦች ናቸው፡፡ አንዳንዶች በአዕምሮ ዕውቀታቸው ደንዝዘው ደንቁረዋል፡፡›› በማለት ይተነትናል፡፡
አዎ ትምህርታቸው ያላነቃቸው፤ ማወቃቸው ያልጠቀማቸው፣ መማራቸው ያላሰለጠናቸው፤ ለወገናቸው ጠብ የሚል መላ ያልፈጠሩ ጠብደል ደደቦችን ዩንቨርስቲ ይቁጠራቸው፡፡ እያወቁ የማያውቁ፣ እያዩ የማያዩ፣ እየሰሙ የማይሰሙ የደነዘዙ አድርባይ ምሁራን እልፍ ናቸው፡፡ የዳቦ እውቀታቸው ጨጓራቸው ጋ እንጂ ልባቸው ጋ አይደርስም፡፡ ጥናትና ምርምራቸው ከአንገት በታች ነው፡፡ ጥበባቸው ከርስን መሙላት፣ የዓይን አምሮትን ማርካት፣ ቁስ ማግበስበስ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ድድብና ከወዴት ይገኛል??
ወዳጄ ሆይ... ተወዳጁ አሜሪካዊው ፀሐፊ ማርክ ትዌይን ‹‹ከደደቦች ጋር አትከራከር፡፡ ከደረጃህ አውርደው ከነሱ ተርታ ያሰልፉሃል›› እንዳለው የልብ ዕውቀት ከሌላቸው ሰዎች ጋር እሰጣ-ግባ ውስጥ አትግባ፡፡ እነሱ ሁሉን የሚያውቁ የሚመስላቸው ሞራልና ስነምግባር የሌላቸው አውሬዎች ናቸው፡፡ አንተ ግን በልብህም በአዕምሮህም የበቃህ ሁን፡፡ በሕሊናህም በመንፈስህም ሰልጥን፡፡ በስሜትህም በአዕምሮህም ብሰል፡፡ አለማወቅህን በዕውቀት ደምስሰው እንጂ የተማረ የአዋቂ ደደብ አትሁን!
ቸር ጊዜ!
_____________________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
እሁድ ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.
Ke atnatiose eshetu birru page የተወሰደ